6ኛው ዙር የኦሮሚያ ክልል የባህልና ዝክረ ኪነ ጥበብ መድረክ በጉጂ ዞን በመካሄድ ላይ ነው

63
ዲላ ግንቦት 24/2010 የኪነጥበብ ባለሙያዎች ባህላዊ እሴቶቻችንን ሀገራዊ አንድነትና ልማትን በሚያጠናክር መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እልፍነሽ ኃይሌ ገለፁ፡፡ 6ኛው ዙር የኦሮሚያ ክልል የባህልና ዝክረ ኪነ ጥበብ መድረክ ''ባህላዊ እሴቶቻችን ለሰላማችንና አብሮነታችን'' በሚል መሪ ቃል በጉጂ ዞን በመካሄድ ላይ ነው፡፡ መድረኩን በንግግር የከፈቱት ዋና ዳይሬክተሯ ዶክተር እልፍነሽ ኃይሌ እንደገለፁት ተመሳሳይ መድረክ በየአመቱ መካሄዱ ወጣት የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከአንጋፋዎቹ ልምድና የሙያ ስነምግባር እንዲቀስሙና በወጣቶች ዘንድ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ እገዛ ያደርጋል፡፡ የህዝቡን ባህላዊ እሴቶችም ከአደጋ ለመታደግ ጉልህ አስተዋፅኦዖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ የነበረንን አንድነት፣ አብሮነትና መቻቻል አጠናክሮ ለማስቀጠል ኪነጥበብ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል፡፡ ኪነ-ጥበብ ውስጣዊ ስሜትን ለመግለፅ እንዲሁም የማህበረሰቡን አመለካከት ለመቅረፅ ከፍተኛ አቅም እንዳለው የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ሀገራዊ አንድነትና ልማትን በሚያጠናክር መልኩ ጥቅም ላይ ሊያውሉት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ ዋጋሪ በበኩላቸው መንግስት የለውጥ እርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት ሰዓት መድረኩ መካሄዱ ሀገራዊ አንድነትን ለመመለስ እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡ ''የገዳ ሥርዐት ሞጋሳ እና ጉዲፈቻ የተሰኘ ከሌሎች የሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በአንድነት ለመኖር የሚጠቅም ባህላዊ መስተጋብርን አቅፎ የያዘ ከማይዳሰሱ የሀገሪቱ ቅርሶች አንዱ ነው'' ብለዋል፡፡ መድረኩም ይህን ሥርዐት ለትውልድ ለማስተላለፍና ኢትዮጵያዊ አንድነትን ይበልጥ ለማሳደግ የሚያበረክተው አስተዋፅዖ የላቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በበዓሉ ላይ ከታደሙ የባህል ልዑካን ቡድን አባላት መካከል ከቦረና ዞን የመጣው ወጣት ክንዲሁን አየለ ''መድረኩ የቀድሞ አባቶች እንዴት እርስበርሳቸው ተዋደውና ተቻችለው እንደኖሩ የምንማርበት ነው'' ብሏል፡፡ ከዚህ በፊት ከነበሩ ተመሳሳይ መድረኮች እውቀትና ልምድ መቅሰሙን የተናገረው የጉጂ ዞን የባህል ቡድን አባል ወጣት አብዱልቃድር ሱልጣን በበኩሉ ''የመቻቻልና የአንድነት ባህላችንን ሌሎች ወጣቶች እንዲያውቁት በየአካባቢያችን እየሰራን እንገኛለን'' ሲል ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባህል ማዕከል ከኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ባዘጋጁትና ለስድስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ መድረክ ላይ ከ13 ዞኖችና ስድስት ከተማ አስተዳደሮች በመጡ የባህል ልዑካን ቡድኖች መካከል የኪነ ጥበብ ትርኢትና ውድድር ይካሄዳል፡፡ በክልሉ የኪነጥበብ እድገት ላይ አሻራቸውን ያኖሩ አንጋፋ አርቲስቶችም ይዘከሩበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም