አገራዊ ክብርና ልዕልናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የመከላከያ ሰራዊት የማይተካ ሚና አለው _ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

76
አዲስ አበባ 24/2010 አገራዊ ክብርና ልዕልናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የመከላከያ ሰራዊት የማይተካ ሚና እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ለመከላከያ ሰራዊት ኃላፊዎች በንድፈ-ሃሳብ የታገዘ ገለጻ አድርገዋል። የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅሞች ለማስከበር የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ቴክኖሎጂ፣ ዲፕሎማሲ እና ወታደራዊ አቅሞችን አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚያስፈልግ የገለጹት ዶክተር አብይ፤ 'አገራዊ ክብርና ልዕልናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የመከላከያ ሰራዊት የማይተካ ሚና አለው' ብለዋል። 'ብሄራዊ ፍላጎትና ጥቅም የህዝብ ፍላጎትና ጥቅም በመሆኑ የመከላከያ ሰራዊት ከህገ-መንግስቱ የሚመነጩ ግልጽ ተልዕኮዎችን አንግቦ ለህዝብ ፍላጎትና ጥቅም የሚሰራ መሆን አለበት' ብለዋል፡፡ ከ19ኛውና 20ኛው ክፍለ ዘመን በፊት የመንግስት ምስረታና የአገር ጥቅምና ፍላጎት የሚመነጨው ከገዢ መደቦችና እምነት ተቋማት እንደሆነ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ዘመን ብሄራዊ ጥቅም በህዝብ ፍላጎት ብቻ የተመሰረት መሆኑን አስገንዝበዋል። 'የብሄራዊ አቅማችን ዋነኛ መገለጫ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግቦችን ማሳካትና የአገራችን ህዝቦች ክብርና የአገርን ሉዓላዊነት ማስከበር ናቸው' ብለዋል፡፡ ዘመናዊው ጦርነት ከመደበኛ የጦርነት አውድ የተለየ ቅርጽና መልክ እንዳለው የተናገሩት ዶክተር አብይ፤ የቴክኖሎጂ እድገት መኖርና አለም ዓቀፋዊነት ያመጣው የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና የባህል ትስስር መልኩን የቀየረው መሆኑን አስረድተዋል። ዘመናዊ መደበኛ ጦርነቶች የሚያስከፍሉት ዋጋ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ መንግስታት በቀጥታ ጦርነት ከመግባት ይልቅ የውክልና ጦርነትን መምረጥ መጀመሩን ተናግረዋል። በነገሮችና በሁነቶች መተሳሰር ምክንያት አንድ አካባቢ የሚከሰት ድርጊት አለም ዓቀፋዊ በሆነ መልኩ ቀውስን የሚያስከትልበት ደረጃ መደረሱን መገንዘብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። በነገሮችና በሁነቶች መተሳሰር እጅግ በጠነከረበት በዚህ ዘመን የሚያጋጥሙ ስጋቶችን መረባዊ በመሆናቸው፣ ስጋቶችን መመከት የሚቻለው በመረባዊ አደረጃጀት እንደሆነ ገልጸዋል። 'ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባት መከላከያ ሰራዊቱ ራሱን በቀጣይ የለውጥ ምህዋር ውስጥ ማስገባት አለበት' ብለዋል፡፡ የዚህ ለውጥ መነሻ ሁኔታዎችም የአገሪቱ የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ሁኔታዎችና በአጠቃላይ የህዝብ ስሜት እንደሆነ ገልጸው፤ 'አገራችን በቅርቡ የፖለቲካ አለመረጋጋት በመግባቷ ከፍተኛ አደጋ ያንዣበበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር' ብለዋል። በዚህም 'መንግስት ችግሩን መፍታት አይችልም' እስከማለት የደረሰ ትችት ቢደርስም ተግዳሮቱን ወደ እድል በመቀየር አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን በአፋጣኝ መውሰድ ተጀምሮ የህዝቡን ተስፋ በመመለስ ለውጡን ለማስፋት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል። ሰራዊቱ ሙያዊ ብቃትን፣ ሃላፊነት የመውሰድና የተሟላ ስብዕናን የተላበሰ እንዲሆን ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑንም ተናግረዋል። 'ሙያዊ ብቃቱን ማሳደግ ሰራዊቱ በመርህ የሚገዛና ለወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ተጽዕኖ በቀላሉ እጅ የማይሰጥ የህዝብን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስከብር ያደርገዋል' ብለዋል፡፡ በቅርቡ በተደረገው የመንግስት ስልጣን ሽግግር ወቅት ሰራዊቱ ያሳየውን ሙያዊ ዲሲፕሊን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድንቀዋል። 'በምድር ሀይልና በአየር ሀይል በአፍሪካ ቀደምት አገሮች ተርታ ያስቀመጠንን ሀይል ገንብተናል' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህር ሀይል አቅምን በቀጣይ ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። 'መከላከያ ሰራዊቱ የብሄር፣ ብሄረሰቦች ነጸብራቅ፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት መጽዳት፣ ለሲቪል አስተዳደርና ለህገ-መንግስቱ ተገዥ መሆን፣ የአገርን ሉዓላዊነት የማስከበር ተልዕኮ ያስቀመጠ በመሆኑ የመከላከያ ሰራዊት ህገ-መንገስታዊ ባህሪውን ጠብቆ መዝለቅ አለበት' ብለዋል፡፡ የመከላከያ ሰራዊት ዋነኛ አላማ በሲቪል አስተዳደሩ የሚቀመጡ አገራዊ ስጋቶችና የደህንነት ስጋቶችን በተቀመጠለት ትርጓሜ መሰረት በላቀ ብቃት ግዳጁን የማስፈጸም፣ የህዝብን ፍላጎቶችና ጥቅሞች ማስከበርና የአገር ክብርና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሆነ አስረድተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም