ኦዴፓ 29ኛ የምስረታ በዓሉን “መደማመጥ ለቀጣይ የስኬት ጉዞ” በሚል መሪ ሀሳብ አከበረ

82

አዲስ አበባ መጋቢት 22/2011 የዴሞክራሲ ስርዓት በመገንባት፤ ኢትዮጵያን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ማሸጋገር በቀጣይ የምንታገልለት ነው ሲሉ በልደታ ክፍለ ከተማ የኦዴፓ ዋና ፀሐፊ ወይዘሮ ገነት ቅጣው ተናገሩ።

የክፍለ ከተማው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት 29ኛ የምስረታ እና 1ኛ ዓመት የለውጥ በዓሉን ደጋፊዎቹና አባላቱ በተገኙበት ዛሬ አክብሯል።

ወይዘሮ ገነት በዚሁ ወቅት እንዳሉት ድርጅቱ የዜጎች  እኩልነት የተረጋገጠበትና ዴሞክራሲያዊ የፌደራል ስርዓት የሰፈነባት አገር ለመፍጠር ይሰራል።

ወይዘሮ ገነት አያይዘውም ድርጅቱ ባለፈው ዓመት እንደገና ራሱን በጥልቀት ፈትሾ ሲደራጅ የህግ የበላይነትን፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እና የዴሞክራሲ ሥር -ዓትን ለመገንባት ነው፡፡

ከአጋር ድርጅቶች አዴፓን ወክለው በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ጳውሎስም በዓሉ በእጃችን ላይ ያለውን ድል እንድንጠብቅና ሐገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

እስካሁን ከተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎችም መካከል የፖለቲካ ምህዳሩ  መስፋትን እንደ አብነት አውስተዋል ።  

በዓሉን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የልደታ ክፍለ ከተማ የኦዴፓ ኮሚቴ አባል አቶ ቲኬ ድሪባ ደግሞ በዓሉን የምናከብረው ድርጅቱ የተመሠረተው 29 ዓመት በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ህዝባችን ባለፉት ስርዓቶች ከገጠመው ችግር የወጣበትን መንገዶች በማስታወስና በቀጣይም  የተሻሉ ተሞክሮዎችን ተጠቅሞ አገሪቷን ወደ ፊት ለማስቀጠል ነው ብለዋል።

የፓርቲው አጋሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና ወጣቶች በአንድነት በዓሉን አክብረዋል።

በበዓሉ የመክፈቻ ስነ ስርዓትም በትግሉ ላይ ለተሰውት የህሊና ፀሎት  ተደርጓል  ፣በአገር ሽማግለሌዎችም የምረቃ ስርዓት ተከናውኗል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም