የምስራቅ ወለጋ ዞን ዓመታዊ የስፖርት ሻምፒዮና ውድድር ተጀመረ

42

ነቀምቴ መጋቢት 22/2011 የምስራቅ ወለጋ ዞን 25ኛው ዓመታዊ የልዩ ልዩ ስፖርት ሻምፒዮና ውድድር ዛሬ  በነቀምቴ ከተማ ተጀመረ።

ውድድሩ በነቀምቴ ከተማ ለሚካሄደው የኦሮሚያ ሻምፒዮና ውድድር ዞኑን ወክለው የሚሳተፉ ብቁ ስፖርተኞችን ለመምረጥ  እንደሆነ ተገልጿል፡፡

እስከ መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም.  የሚቆየው ውድድር እግርና እጅ ኳስ፣  ቦሊቦል፣ ጠረጴዛ ቴኒስ ፣ዳርት፣ አትሌትክስና ፓራ ኦሎምፒክ ስፖርት ዓይነቶች የሚካሄድ ነው።

የዞኑ ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ብየና እንደገለፁት ለሳምንት የሚቆየው ውድድሩ በ16 ወረዳዎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር መካከል የሚካሄድ ነው ።

በውድድሩ ከሚሳተፉ 602 ስፖርተኞች መካከል 133  ሴቶች ናቸው፡፡

"ተሳታፊዎች የስፖርቱን ስነ- ምግባር በመጠበቅ በፍቅር፣ በመደመርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ ውድድር ማካሄድ ይጠበቅባችኋል" ሲሉ ያሳሰቡት ደግሞ የዞኑ  ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አስመራ እጃራ ናቸው።

በመክፈቻው ስነ ስርዓት ወቅት በተካሄደ የ5 ሺህ ሜትር የወንዶች ሩጫ ውድድር ዋዩ ቱቃ፣ጅማ አርጆና ሊሙ ወረዳዎች በተሳታፊዎቻቸው ከአንደኛ እስከ ሶሰተኛ በመውጣት የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።

በሴቶች 3 ሺህ ሜትር ሩጫም ዋዩ ቱቃ ወረዳን ወክለው የተሳተፉ  ተወዳዳሪዎች  ከአንደኛ እስከ ሶሰተኛ ተከታትለው በመግባት የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም