የትምህርት ፍኖተ ካርታው ለአገራዊ ለውጥ ና ዕውቀት ሊያበረክት ይገባል ---ባለሞያዎች

100

አዲስ አበባ መጋቢት 22/2011 የትምህርት ፍኖተ ካርታው አገር በቀል ዕውቀትን ከውጭ ዓለም ጋር ያጣጠመ መሆን እንዳለበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የትምህርት ባለሙያዎች ተናገሩ።

የትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ በአገር በቀል ይዘቶች የተቃኘና አገራዊ ለውጡን በሚያግዝ መልኩ የተቀረጸ መሆኑን አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ትምህርትና ስነ ባሕሪ ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የስርዓተ ትምህርት ምሁሩ ዶክተር ውቤ ካሳዬ፤ ስርዓተ ትምህርት ለትምህርት ዘርፉ አንኳር ጉዳይ ነው ይላሉ።

የስርዓተ ትምህርት ውጤታማነት የሚለካው በተከታታይና አጠቃላይ ግምገማ ተካሄዶ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ውቤ፣ ይህ ካልሆነ ግን የትምህርቱን ደረጃ ለማወቅም ሆነ መንግስታዊ ውሳኔ ለመስጠት አስቸጋሪ ነው ይላሉ።

አሁን በስራ ላይ የሚገኘው ስርዓት ትምህርት ግን በየጊዜው ከሚደረጉ ትናናሽ ጥናቶች በስተቀር ለ27 ዓመታት አጠቃላይ ግምገማ ሳይደረግበት የቆየ በመሆኑ አሉታዊ ጎኑ ያይላል።

የመምህራን ስልጠና፣ የትምህርት አስተዳድርና ፍልስፍናው መሰረቱ ስርዓተ ትምህርቱ መሆኑን ገልጸው፤ ዘግይቶም ቢሆን ጥናትና ምርምር መደረጉና የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ መጀመሩ መልካም ተግባር ነው ባይ ናቸው።

ከነሐሴ 2010 ዓ.ም ጀምሮ ውይይቶች እየተደረጉበት ያለው የፍኖተ ካርታው ረቂቅ የአገር በቀል ዕውቀቶችና እሴቶችን ማካተትና ከውጭ የመጣውንም በማካተት ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ ማስኬድ እንዳለበት ነው የሚናገሩት።

አድዋን ለአብነት የሚያነሱት ዶክተር ውቤ ከአፍሪካዊያን ጋር የሚያስተሳስሩ እንደ ቋንቋ፣ያሬዳዊ ሙዚቃ፣ ገዳ ስርዓት፣ ፊደል፣ ታሪክና መሰል ጉዳዮችን ስርዓተ ትምህርቱ ሊመለከተው እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ደበበ ገብረ ጻድቅ ባለፉት 27 ዓመታት ስራ ላይ የቆየው ስርዓተ ትምህርት የራሱ በጎ ነገር ቢኖረውም ሳይከለስ ለአንድ ትውልድ ጊዜ ያህል መዘግየቱ ግን ውስንነቱ እንደነበረ ተናግረዋል።

መምህራን ስርዓተ ተምህርቱ እንዲከለስ በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ አገሪቷ የገጠማት ወቅታዊ የትምህርት ጥራት ችግር ምናልባትም በወቅቱ ቢከለስ እንደዚህ  የከፋ አይሆንም ነበር ይላሉ።

ስርዓተ ትምህርቱ የውጭ ትምህርቶች ቤተ ሙከራ መሆን እንደሌለበት በመግለጽ፣ አገራዊ አንድነትና ፍቅር ያለው ትውልድ ለመቅረጽ አገር በቀል ዕውቀቶችና የስነ ትምህርት ፍልስፍናዎችን የያዘ መሆን እንዳለበት ነው የተናገሩት።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲም ስርዓተ ትምህርት በቅድሚያ አገር አቀፍ ወግ፣ እሴትና ታሪክን ያካተተ፤ አገራዊ ነጸብራቅ ያለው ስርዓተ ትምህርት መሆን እንዳለበት አብራርተዋል።

ስርዓተ ትምህርቱ አገሪቷ አሁን ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አገራዊ ለውጡን የሚያግዝ እንደሆነም ነው የትምህርት ባለሙያዎቹ የሚናገሩት።

አገራዊ ለውጥ የሚመጣው በትምህርት እንደሆነ በመጥቀስ፣ ስርዓተ ተምህርት አገሪቷ በቀጣይ አስር ዓመታት የምትመራበት በመሆኑ ከመንግስት ሰርዓት ጋር ሳይሆን አገሪቷን ወደፊት ሊያራምድ በሚችልና ትውልድ በሚቀርጽ አግባብ መዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅትና ትግበራ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ሸዋርገጥ ፍኖተ ካርታ ለአገር ብልጽግና የሰው ሃይል ለማፍራት የሚያገለግል መሳሪያ ነው ይላሉ።

በጊዜ ሳይከለስ የረፈደበት የወቅቱ ስርዓተ ትምህረትን ለመገምገም አጠቃላይ ትምህርትና ስልጠና ችግሮቹን የዳሰሰና ምክረ ሀሳብን ያካተተ የረጂም ጊዜ ጥናት መደረጉንም ተናግረዋል።

ሰርዓተ ትምህርቱም ለአገራዊ አንድነትና አብሮነት የሚበጁ አገራዊ ባህልን፣ ታሪክን፣ አገር በቀል ዕውቀትንና ግብረ ገብነትን ያካተተ ሆኖ መቀረጹን አመልክተዋል።

በየትኛውም መስክ የሚደረግ አገራዊ ለውጥ ፍሬያማ የሚሆነው ተወዳደሪና ብቁ የሰው ኃይል ሲኖር ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ስርዓተ ትምህርቱ ለወቅቱ አገራዊ ሪፎርም መጠናከር ያለው ሚና ከፍተኛ ነው።

በታዋቂ ምሁራን የተደረገ አጠቃላይ ጥናቱ ሶሰት ዓመታትን የፈጀው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ካለፈው ነሃሴ 2010 ዓ.ም ጀምሮ በረቂቁ ላይ ምሁራን፣ የትምህርት ማህበረሰብና ህዝቡ ውይይት  ቆይቷል።

ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ በፍኖተ ካርታው ላይ የትምህርትና ስልጠና ማኅበረሰብ ውይይት ተደርጎበት የተጠናቀቀ ሲሆን በሁለተኛ ዙር ደግሞ በፌዴራልና በክልል ተቋማት ሰራተኞችና ባለሙያዎች ውይይት እየተደረገበት መሆኑ ተጠቁማል።

እስካሁንም ከ844 የትምህርትና ስልጠና ባለሙያዎች፣ 15 ሺህ የፌዴራል፤ ከ3 ሚሊየን በላይ ደግሞ የክልል ተቋማት ሰራተኞች በውይይቱ መሳተፋቸውን የሚኒስቴሩ መረጃዎች ያሳያሉ።

በፍኖተ ካርታው ከባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ምክር ቤት የተቋቋመለት ሲሆን በውይይቱ የሚሰበሰቡ ግብዓቶች ተካተውበት መጨረሻ ላይ ለመንግስት ቀርቦ ይሁንታ ሲያገኝ ይጸድቃልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም