ተፈናቃይ ነን በማለት በጅማ ህብረተሰቡን ያጭበረበሩ ሁለት ግለሰቦች ተቀጡ

121

ጅማ መጋቢት 22/2011 ከወለጋ እንደተፈናቀሉ በማስመሰል በጅማ ከተማ ህብረተሰቡን በማጭበርበር እርዳታ ሲያሰባስቡ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ሁለት ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ   መቀጣታቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እንደገለጸው  ግለሰቦቹ  ከወለጋ እንደተፈናቀሉና ቤታቸው ንብረታቸው እንደተወሰደ በመናገር በሀሰት  ከህብረተሰቡ  ለአምስት ቀን እርዳታ ሲያሰባስቡ ቆይተዋል።

ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ  በግለሰቦቹ ላይ ባደረገው ክትትል የካቲት 22/ 2011ዓ.ም. በጅማ ቢሺሼ የገበያ ማዕከል እንደያዛቸው የመምሪያው የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ኢንስፔክተር ገዛኸኝ  አውጋቸው ለኢዜአ  ተናግረዋል።

"በወንጀል ድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉት ሁለቱ ግለሰቦች  ነዋሪነታቸው  አዲስ አበባ መሆኑ በተደረገባቸው ምርመራ ተረጋግጧል" ብለዋል።

በሃሰት ካሰባሰቡት ገንዘብ ውስጥ አንደኛው መኪናውን እንድታሰራለት  5 ሺህ 300 ብር ለባለቤቱ መላኩንና ሌላኛው ደግሞ 3 ሺ 23 ብር ለዘመዶቹ መላኩን በሰጡት የእምነት ቃል አረጋግጠዋል።

ከዚህ ገንዘብ በተጨማሪም ፖሊስ በግለሰቦቹ  እጅ   አራት ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ በኢግዚቢትነት መያዙንም አመልክተዋል።

በወንጀል ተከሰው ጉዳያቸውን ሲከታተል የቆየው የጅማ ዞን  ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰሞኑን በዋለው ችሎች እያንዳንዳቸው በአንድ ዓመት ከስምንት ወራት ጽኑ እስራትና በ500 ብር እንዲቀጡ የወሰነባቸው መሆኑን ኢንስፔክተሩ ገልጸዋል።

ግለሰቦች ክስቸውን እንዲከላከሉ እደሉ ቢሰጣቸውም ባለመቻላቸው የቅጣት ውሳኔው ጸንቶባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም