የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲው ለሚከፍተው ተጨማሪ ካምፓስ ያልተጠናቀቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ተረከበ

282

ሶዶ መጋቢት 22/2011 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በቦዲቲ ከተማ ለሚከፍተው ተጨማሪ ካምፓስ ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ 20 የጋራ መኖሪያ ቤት ህንጻዎችን ተረከበ ።

ዩኒቨርሰቲው የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን የተረከበው ከክልሉ ኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ላይ ነው ።

ዩኒቨርሲቲው በዘጠኝ ሄክታር መሬት ላይ ያረፉትን ጅምር ህንጻዎች 25 ሚሊዮን ብር በመክፈል ነው የተረከበው።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል ኮንስትራክሽንና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ አቶ ክፍሌ ገብረማሪያም በርክክብ ስነ ስርዓት ወቅት  እንዳሉት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተጀምረው ሳይጠናቀቁ የቆዩ የጋራ መኖሪያ ህንጻዎች በህዝብ ዘንድ ቅሬታ ሲያስነሳ ቆይቷል።

“የጋራ መኖሪያ ህንጻዎቹ የመኖሪያ የቤት ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች ግንባታቸው በመጀመሩ ሳይጠናቀቁ ለረዥም ዓመታት እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል” ብለዋል ።

በተፈጠረው ስህተት የሀብት ብክነት እንዳይደርስ ዩኒቨርሲቲው እንዲረከባቸው መደረጉን ተናግረዋል ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታከለ ታደሰ በበኩላቸው የትምህርት ስራውን ተደራሽ ለማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች ካምፓሶችን ለመክፈት ዕቅድ ተይዞ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

“በጅምር የቆዩ ህንጻዎችን ለመማር ማስተማር ስራው አመቺ በሆነ መልኩ በማጠናቀቅ በመጪው ዓመት ስራ እንዲጀምሩ ይደረጋል ” ብለዋል ።

የካምፓሱ መከፈት በቦዲቲ ከተማና አካባቢው ለልማት እንዲሁም ለምጣኔ ሀብት መነቃቃት አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ህብረተሰቡ ለስራው ስኬታማነት የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግም ምልዕከታቻወን አስተላልፈዋል።

የቦዲቲ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዘካሪያስ ጃታ ህንጻዎቹ በጅምር በመቆየታቸው የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከመሆን ባለፈ የወንጀለኞች መመሸጊያ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ በዳውሮ ዞን ተርጫ ከተማ ተጨማሪ ካምፓስ መክፈቱ ይታወሳል።