በዴንማርክ በተደረገው የአለም አገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵያ አጠቃላይ አሸናፊ ሆነች

78

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2011 ኢትዮጵያ በዴንማርክ አርሁስ ከተማ በተደረገው የአለም አገር አቋራጭ ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ ሆነች።

ኢትዮጵያ በውድድሩ 5 የወርቅ 3 የብርና 3 የነሃስ ሜዳሊያ በድምሩ 11 ሜዳሊያ በማግኘት ነው በበላይነት ማጠናቀቅ የቻለችው።

ኬኒያ በ 2 ወርቅ 3 ብርና 3 ነሃስ ሜዳሊያ ሁለተኛ ወጥታለች።

ውድድሮቹ በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ሴት 6 ኪሎ ሜትርና በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ የዱላ ቅብብል ተካሂዷል።

በዚህም በአዋቂ ወንዶች 10 ኪሎ ሜትር የኡጋንዳዎቹ ጆሺዋ ቺፕቴጌና ጃኮብ ኪፒሊሞ ተከታትለው ሲገቡ ኬኒያዊው ጂኦፈሪ ኮሞሮሮ ሶስተኛ ወጥቷል።

በውድድሩ የአሸናፊነት ቅድሚያ ግምት የተሰጠው ሰለሞን ባረጋ አምስተኛ ወጥቷል።

በአዋቂ ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ሄለን ኦብሪ ከኬንያ ቀዳሚ ሆና ስትገባ ደራ ዲዳና ለተሰንበት ግደይ ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።

ከሀያ አመት በታች ወጣት ወንዶች 8 ኪሎሜትር ሚልኬሳ መንገሻ ቀዳሚ ሲሆን ታደሰ ወርቁ ሁለተኛ ሆኗል።ከ20 አመት በታች ሴቶች 6 ኪሎሜትር ቤትሪሲት ቺሌት ከኬንያ ቀዳሚ ስትሆን አለሚቱ ታሪኩ ሁለተኛ ጽጌ ገብረሰላም ሶስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ ውድድር ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆናለች።

ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት በኡጋንዳ ርዕሰ መዲና ካምፓላ በተካሄደው 42ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በ4 የወርቅ፣ በ4 የብርና በ1 የነሐስ በድምሩ ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።

ኬንያ በሻምፒዮናው 4 የወርቅ፣ 5 የብርና 3 የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አሸናፊ መሆኗ አይዘነጋም።

የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ አገራት እየተካሄደ የሚገኝ ውድድር ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ በዚህ ሻምፒዮና እየተካፈለች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም