አየር መንገዱ በቱሪዝም መስክ የያዘው ራእይ እንዲሳካ ድጋፍ እናደርጋለን-የአሜሪካ አስጎብኚዎች ማህበር

59

አዲስ አበባ መጋቢት 21/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቱሪዝም መስክ የያዘው ራእይ እንዲሳካ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን የአሜሪካ አስጎቢኚዎች ማህበር ገለጸ።

የማህበሩ ከፍተኛ የስራ አስፈፃሚዎች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመሆን በአገሪቷ ያደረጉትን የቱሪስት መዳረሻዎች ጉብኝትና በቀጣይ ሊሰሩት ስላሰቧቸው ጉዳዮች ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህ ጊዜ የማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቴሪ ዳኒ በኢትዮጵያ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ማዘናቸውን ገልጸው ለአደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።

አየር መንገዱ በቅርቡ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ መባሉ የሚያስደስት ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ።

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ባሏት እምቅ የቱሪዝም ሃብቶች ከአለም 10 መዳረሻዎች አንዷ ብትሆንም ያሉትን የቱሪዝም ሃብቶች በማስተዋወቅና በማስተማር በኩል ከፍተኛ ክፍተት ይታያል።

በዚህም ጎብኚዎችን በሚፈለገው ደረጃ ለማምጣት እንዳልተቻለ ጠቅሰው በአገሪቷ ባለፉት ቀናት ተዘዋውረው በተመለከቱት መሰረት በቀጣይ የጎብኚዎቹ ቁጥር እንዲጨምር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ማህበሩ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው 99 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሀብት ያለው ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ 9ነጥብ5 ሚሊዮን ቱሪስቶች የቱሪስት መስህቦችን እንዲጎበኙ እያደረገ ይገኛል።

በተጨማሪ በአመት ለቱሪስቶቹ 5ነጥብ4 ሚሊዮን የአየር መንገድ ትኬት ይገዛል።

አባላቱ በጉብኝታቸው አገሪቷ ለቱሪዝም መዳረሻነት ያላትን አመቺነት፣ ሰላምና ጸጥታ፣ የአውሮፕላን ብዛት፣ መዳረሻና የመሳሳሉትን እምቅ አቅም መገንዘብ እንደቻሉ ተናግረው በቀጣይ በዘርፉ የኢትዮጵያን ድርሻ ከፍ ለማድረግ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የአሜሪካ አስጎቢኚዎች ማህበር በአሜሪካ ትልቅ ተቋምና በርካታ አባላት ያሉት ብቻ ሳይሆን የጎብኚዎች ምንጭም ነው።

''የማህበሩን አቅም ለመጠቀም፣ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅና ስለ ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማስተማር በጋራ እንሰራለን'' ብለዋል።

ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ለማስተዋወቅና መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ውጤታማ ለማድረግ ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል።

አየር መንገዱ ከሆቴሎችና ከአስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ጥራቱን የጠበቀ፣ ተወዳዳሪና ተመጣጣኝ አገልግሎት እንዲኖር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ባደረገችው የማግባባት ስራ የአሜሪካ አስጎቢኚዎች ማህበር አመታዊ ስብሰባውን በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አዲስ አበባ ላይ  ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም