የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው

80

ሰቆጣ  መጋቢት 21/2011 የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች ጋር በሰቆጣ ከተማ እየተወያዩ ነው፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በሪሁን ኪዳነማሪያም ውይይቱ ችግሮችን በጋራ ተግባብቶ ለመፍታት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ወጣቱ ለሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከከፍተኛ አመራሩ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ መወያየት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም አመልክተዋል።

ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ የበርካታ ፀጋዎች ባለቤት ቢሆንም ያሉትን ፀጋዎች በተሻለ ቴክኖሎጂና እውቀት አልምቶ በመጠቀም በኩል ክፍተት መኖሩን አቶ በሪሁን ተናግረዋል።

የፋብሪካዎች አለመስፋፋት፣ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እጥረት በብሔረሰቡ አስተዳደር መኖሩንም አንስተዋል።

"ውይይቱ እነዚህንና በአስተዳደሩ ያሉ መሰል ችግሮች ላይ ለመነጋገርና ከለውጡ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ጥርጣሬዎችን አስወግዶ በቀጣይ መፍትሄ ለማስቀመጥ ወሳኝ ነው" ብለዋል።

የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ አቶ ቴድሮስ ጨርቆሴ በበኩላቸው በብሔረሰብ አስተዳደሩ ያለውን የብረት ማዕድን ለማዕልማት በማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኩል ከኩባንያዎች ጋር ውል ቢገባም አስካሁን ወደ ሥራ አለመገባቱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።

ከኮረም-ሰቆጣ-አብዓዲ የአስፓልት መንገድ ይሰራል ተብሎ ቃል ቢገባም አስካሁን ተፈጻሚ እንዳልሆነ ጠቁመው "እየተሰሩ ያሉ መንገዶችም በወቅቱና በጥራት እየተገነቡ አይደለም" ብለዋል።

የሰቆጣ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እንዲሁም የዳስ እና የዛፍ ጥላ ስር ትምህርት ቤቶች በክልሉ መንግስት ተገቢ ትኩረት እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

በከተማው ደረጃውን የጠበቀ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከልና ሪፈራል ሆስፒታል እንዲገነባ የጠየቁት ሌላው የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ተልካ ካሴ ናቸው። 

"የብሔረሰብ አስተዳደሩ እስካሁን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተጠቃሚ ባለመሆኑ መንግስት ለጥያቄያችን ምላሽ ሊሰጠን ይገባል" ብለዋል።

በህብረተሰቡ በኩል ለተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በርዕሰ መስተዳደሩ ዶክተር አምባቸውና በሌሎች የክልሉ አመራሮች በኩል ምላሽ ይሰጥባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም