አሲዳማ መሬትን ለማከም ኖራን ብቻ ሳይሆን ባህላዊ ዘዴዎችንም መጠቀም ውጤታማ ያደርጋል…የዘርፉ ምሁር

272

ወልዲያ መጋቢት 21/2011 አርሶ አደሩ በአሲድ የተጠቃን የእርሻ መሬት ለማከም ኖራን ብቻ ሳይሆን ባህላዊ ዘዴዎችንም ቢጠቀም ውጤታማ እንደሚሆን በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ አንድ የዘርፉ ምሁር አስታወቁ፡፡

በዩኒቨርሲቲው መርሳ ግብርና ካምፓስ የአፈር ሳይንስ ተመራማሪና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር እንዳልካቸው ፈቃዱ ለኢዜአ እንዳሉት ባለፈው ዓመት ባካሄዱት ምርምር ከፍተኛ አሲዳማ አፈር መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡

ምርምራቸውን በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ በ2ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ማድረጋቸውንና በሰሜን ወሎ ደጋማ አካባቢዎች ያለው የአሲዳማ አፈር ሁኔታም ተመሳሳይ መሆኑን ገልጸዋል። 

በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀደም ሲል የተደረገ ጥናት ከሚታረሰው መሬት 40 ከመቶ አሲዳማ መሆኑን እንደተረጋገጠ የገለጹት ፕሮፌሰር እንዳልካቸው፣ አሲዳማ አፈር ምርትን መቶ በመቶ ሊያጠፋ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

” አሲዳማ አፈርን በኖራ ማከም የተሻለ መፍትሄ ቢሆንም በቂ ኖራ ማግኘት እንደማይቻልና ቢገኝ እንኳ ብዙ ኖራ ገዝቶ ለመጠቀም ከአርሶ አደሩ አቅም ጋር ስለማይሄድ ባህላዊ አማራጮችን መጠቀም ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

ለዚህም አነስተኛ መጠን ያለው ኖራ ከተፈጥሮ ማዳበሪያ ጋር በመቀላቀል መጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት አንዱ አማራጭ መሆኑን ባካሄዱት ጥናት ማረጋገጣቸውን ነው የገለጹት፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ ጥራቱን የጠበቀ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ብቻ መጠቀም በራሱ አሲዱን በመቋቋም ምርትን በእጥፍ እንደሚያሻሽል በጥናት መታወቁን ነው የገለጹት፡፡

በተጨማሪም ከሰልና አመድን ከአሲዳማ አፈር ጋር በመቀላቀል መጠቀም ለምርታማነት አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት ፕሮፌሰር እንዳልካቸው፣ ” አሲዳማ አፈር ላይ የፋብሪካ ማዳበሪያን መጠቀም ምርትን ቢጨምርም የመሬቱን አሲዳማነት ያባብሰዋል” ብለዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ እንድሪስ ፈንታው በበኩላቸው ዘንድሮ በ1 ሺህ 250 ሄክታር መሬት ላይ 1 ሺህ 700 ናሙናዎችን በመውሰድ በደሴ የአፈር ላቦራቶሪ ምርመር እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በምርምሩ የሚገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግ ለማከሚያ የሚሆን ኖራ በማስመጣት መሬቱን የማከም ሥራ እንደሚከናወን ነው የተናገሩት።

“በዚህም ከ2 ሺህ በላይ አባውራ ገበሬዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ” ብለዋል፡፡

አቶ እድሪስ እንዳሉት በደጋማው አካባቢ የአፈሩ ጠቃሚ ንጥረ ነገር በዝናብ ታጥቦ መሄድና አፈሩ በተፈጥሮ አሲዳማ መሆን ለአሲዳማ መሬት መኖር ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን አንጎት ወረዳ የቀበሌ ሁለት ነዋሪ አርሶ አደር አበበ በላይ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት ከመሬታቸው ናሙና ተወስዶ አሲድ መኖሩ ቢረጋገጥም ማከሚያ ኖራ ማግኘት ባለመቻላቸው ባህላዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ምርታቸውን ለማሻሻል እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ 10 ሜትር ኩብ ኮምፖስት በማዘጋጀትና ከአፈሩ ጋር በመቀላቀል ከመጠቀማቸውም ሌላ የከብት ሽንትን መጠቀም መፍትሄ ሆኖ እንዳገኙት አስረድተዋል፡፡

በዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ሽመልስ አደራ በበኩላቸው ለምነቱ የተሟጠጠውን ማሳቸውን ለማዳን በየዓመቱ እስከ 15 ሜትር ኩብ ኮምፖስት እያዘጋጁ ማሳቸው ላይ በማፍሰስ ምርታቸውን በእጥፍ ማሳደግ እንደቻሉ አስታውቀዋል።