በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ የብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበራት ሴቶችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው

65

ሰቆጣ መጋቢት 21/2011 በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሴቶችን መሰረት አድረገው የተቋቋሙ የብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበራት የሴቶችን የኢኮኖሚ ችግር እያቃለሉ መሆናቸውን ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡

በዞኑ ዝቋላ ወረዳ ፅፅቃ ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ ፈትለ አየለ ለኢዜአ እንደተናገሩት በ2004 ዓ.ም ከአካባቢያቸው 21 ሴቶች ጋር በመሆን የብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበር አቋቁመዋል፡፡

የሕብረት ሥራ ማህበሩን በወር 50 ብር  በመቆጠብ እንደጀመሩና በአሁኑ ወቅት የማህበሩ ካፒታል 800 ሺህ ብር መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በማህበሩ የቁጠባ ባህላቸውን ከማሳደግ ባለፈ 50 ሺህ ብር ብድር ወስደው ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል።

" ከማህበሩ በወሰድኩት ብድር ሁለት ላምና አምስት ፍየሎችን በመግዛት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በእንስሳት እርባታ ሥራ ተሰማርቻለሁ" ብለዋል፡፡

በእንስሳት እርባታው ከሚያገኙት ገቢ የተበደሩትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ መክፈል ከመቻላቸው ባለፈ ሁለት ክፍል መኖሪያ ቤት መስራታቸውንም ተናግረዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም 22 ሴቶች በጋራ ሆነው የብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበር ማቋቋማቸውን የተናገሩት ደግሞ የጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ስንዱ ጌታወይ ናቸው፡፡

ማህበሩ ለአባላቱ በአነስተኛ ወለድ የብድር ተጠቃሚ የሚሆኑበት ስርአት በመዘርጋቱ የነበረባቸው የገንዘብ እጥረት በአሁኑ ወቅት መቀረፉን ገልጸዋል፡፡

" ከማህበሩ ባገኘሁት 20 ሺህ ብር ብድር ምግብ ቤት ከፍቼ እየሰራሁ ነው " ያሉት ወይዘሮ ስንዱ ሰርተው በሚያገኙት ገቢም ብድራቸውን በመክፈል ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የሩባሪያ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ትበር ገብሩ በበኩላቸው በሴቶች የብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበር ላይ በመሳተፋቸው የህል ንግድ ሥራቸውን ለማሻሻል እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

"ማህበሩ በተለይ በገጠር አካባቢ ያለን ሴቶች የምናገኛትን ገቢ በአግባቡ ቆጥበን እንድንጠቀም ድጋፍ የሚያደርግ በመሆኑ የገንዘብ ችግራችን እየተቃለለ መጥቷል" ብለዋል።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች መምሪያ የሴቶች ግንዛቤና ንቅናቄ ማስፋፊያ ባለሙያ አቶ በሪሁን ታመነ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት ሴቶችን መሰረት ያደረጉ ዘጠኝ የብድርና የቁጠባ ሕብረት ስራ ማህበራት መቋቋማቸውን ተናግረዋል፡፡

"ሴቶች በመንደር ልማት ቡድንን መሰረት በማድረግ ይቆጥቡ ከነበረው አሰራር ወጥተው ህጋዊና ቅንጅታዊ አሰራርን እንዲያገኙ ለማስቻል በብድርና ቁጠባ ማህበራት ስር እንዲቋቋሙ ተደርጓል" ብለዋል፡፡

በእነዚህ ማህበራት የታቀፉ 228 ሴቶች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በመቆጠብ የብድር ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉም አመልክተዋል።

አቶ በሪሁን እንዳሉት ሴቶችን መሰረት አድርገው የተቋቋሙት የብድርና ቁጠባ ማህበራት የሴቶችን የገንዘብ እጥረት በመፍታት በማህበራዊና በኢኮኖሚያ እንዲጠቀሙ እያደረጉ ነው፡፡

በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሴቶችን የብድርና ቁጠባ ማህበራትን ጨምሮ በሁሉም ቀበሌዎች ከ132 በላይ የብድርና ቁጠባ ማህበራት መቋቋማቸውን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ሕብረት ሥራ ማህበራት ፅህፈት ቤት ባለሙያ አቶ አክሊሉ ገብረሕይወት ናቸው፡፡

የብድርና ቁጠባ ማህበራትን መሰረት በማድረግ ባለፉት ዓመታት ከዘጠኝ ሺህ በላይ ሴቶችን የብድር ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ የጠቀሱት ባለሙያው በዚህ ዓመትም 2 ሺህ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አቶ አክሊሉ እንዳሉት ሴቶች በወሰዱት የገንዘብ ብድር በእንስሳት እርባታ፣ በአነስተኛ ንግድና በሌሎች የኑሮ ማሻሻያ ተግባራት ላይ መሰማራት ችለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም