በሰሜን ሽዋ ዞን ከ391 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተከናወነ

146
ደብረ ብርሃን ግንቦት 24/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተያዘው ዓመት 391 ሚሊዮን 758 ሺህ ብር የሚገመት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በአርሶ አደሮች ተሳትፎ መከናወኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የአፈርና እርጥበት እቀባ ባለሙያ አቶ ወንድምነው ክንዴ ለኢዜአ እንደገለጹት የዞኑ አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራውን ያከናወኑት ከ40 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ነው። በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ 6 ሚሊዮን 502 ሺህ አርሶ አደሮች የተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ታውቋል። በአርሶ አደሮቹ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የእርከን ሥራ፣ ክትር፣ የተራቆቱ የተራራ መሬቶችን ከልሎ ማልማት፣ መንከባከብና ችግኝ የመትከል ሥራ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው በዞኑ የሚገኙ 239 ተፋሰሶችም ከእንስሳትና ሰው ንክኪ ነጻ እንዲሆኑ መደረጉን አቶ ወንድምነው ተናግረዋል፡፡ በዞኑ በየዓመቱ በሚከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የተጎዱ መሬቶች ማገገማቸውን የገለጹት አቶ ወንድምነው፣ በአካባቢው የደረቁ ምንጮች ማገገም መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ በሀገረማሪያም ወረዳ የጎርፌ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቄስ ንጉሴ ገብረመስቀል በበኩላቸው በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው በየዓመቱ በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው በማሳቸው ላይ እርከን፣ ክትርና ችግኝ ተከላ ሥራ በማከናወን የአፈር ለምነትን በመጠበቃቸውና የግብርና ግብአት መጠቀም በመጀመራቸው ምርታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ሲል ከሁለት ሄክታር መሬት ከ20 ኩንታል በታች የጤፍ ምርት ያገኙ የነበረው በአሁኑ ወቅት ወደ 50 ኩንታል ማሳደግ መቻላቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል። የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ምርታማ ከማድረጉ ባለፈ መሬታቸው በጎርፍ እንዳይሸረሸር የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። የወይንበር ቀበሌ ነዋሪ አቶ የሺጥላ ሹሜ በበኩላቸው እርከን በተሰራባቸው አካባቢዎች ሣርና የተለያዩ ችግኞችን በመትከል ለከብቶቻቸው መኖ በቀላሉ ለማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል። የግብርና መምሪያ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ በዞኑ ባለፈው ዓመት በአርሶ አደሮች ጉልበት በ60 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተከናውኗል፡፡ በዞኑ በየዓመቱ  የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ክብካቤ ሥራ የሚከናወንባቸውን 1 ሺህ 54 ተፋሰሶች በአግባቡ አልምቶ ለመጠቀም  ህገ-ደንብ ወጥቶ መጽደቁ ለማወቅ ተችሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም