ኢትዮጵያ የወደፊቷ አለም ብሩህ ጉዳይ መታያ

97

/ኢዜአ ሞኒተሪንግ /

ኢትዮጵያ በመፃኢው የአለም እጣ ፈንታ ውሳኔ ላይ ትልቅ ሚና ሊኖራት የምትችል ሃገር ናት። በአለም 1.1 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋትን በመያዝ የ26ተኛ ደረጃን እንዲሁም በ110 ሚሊዮን የህዝብ ብዛቷ  ከምድራችን 12ተኛዋ ግዙፍ ሃገር ናት ኢትዮጵያ፤ ለሁለት ሳምንታት ከደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ጋር ተያይዛ ብቻ ልትነሳ  አይገባትም፤ ሲል ነው ኬንያዊ ጋዜጠኛ ማቲው ኦቲየኖ መርካቶርኔት በተባለ ድረ ገፅ ላይ ምስክርነቱን የሰጣት።  

ጋዜጠኛው ሲቀጥልም አንዳንዶች ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ክስተት በፊት ከነበረው በ1980ዎቹ የቦብ ጌልዶፍ ባንድ ካካሄደለትና በሃገሪቱ ከተከሰተው ድርቅና ረሃብ ዕርዳታ ዘመቻ ጋር ብቻ ሃገሪቷን አያይዘው እንደሚያነሷት ጠቅሶ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከነሱ ሃሳብ የዘለለ የበርካታ ታሪኮች ባለቤት መሆኗን ያነሳል።  

ኢትዮጵያን ሳንወድ በግድ እንድናወራላት የሚገቡም ፈርጀ ብዙ መጠሪያዎች አሏት ያለው ጋዜጠኛው ለአብነትም የሀገሪቷ ምጣኔ ሃብት እኤአ ከ2005 አንስቶ ከ10 በመቶ በላይ ዕድገትን ሙጥኝ ብሎ እንደተጓዘ ጠቁሟል። በ2017ትም በአፍሪካ ገዘፍ ያለ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ካስመዘገቡ ሰባት ሃገራት አንዷ ለመሆን ችላ እንደነበር አስታውሶ፤ ይህም ሁኔታ ሃገሪቷን ‘የአፍሪካ ቻይና’ የሚል ስያሜን እንዳሰጣት መስክሯል። የኢትዮጵያ አየር መንግድም በ112 አውሮፕላኖቹ በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ እንደሆኑት ተርኪሽ ኤርላይንስ፣ ኤይር ፍራንስ እና ብሪቲሽ ኤይርዌይስ ሁሉ ወደ በርካታ የአለማችን ሃገራት የመብረር ብቃትን ያዳበረ እንደሆነም ማቲው ኦቲየኖ ፅፏል።

በቅርቡም መቀመጫውን በዋሺንግተን ዲሲ ያደረገውና በምጣኔ ሃብታዊና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች  ዙሪያ  የተለያዩ  ሪፖርቶችን  በማውጣት የሚታወቀው  ብሩኪንግስ  በተሰኘው  ተቋምEthiopia: Africa's Next Powerhouse? በሚል ርዕስ በድረ-ገጹ  ተንተን ተደርጎ በቀረበው ፅሁፉ ላይ ኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገቷን ለማስቀጠል እየወሰደቻቸው የሚገኙ እርምጃዎችን አስፍሯል።

እንደ ፅሁፉ ሃገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባት ቀዳሚ ተግባሯ በማድረግ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የውጭ መዋዕለ ንዋይን በመሳብ ላይ ትገኛለች። በዚህም ረገድ ኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኩባንያዎች ወደ ሃገሪቱ በመግባት የወጪ ንግድ ገበያው እንዲነቃቃ እያደረገች ነው። በአሁኑ ወቅት አምስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በስራ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን የገለፀው ፅሁፉ ለ45ሺ ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል እንዳመቻቸ ጠቁሟል። ሃገሪቷ እአአ በ2025 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ቁጥር 30 በማድረስ ተጨማሪ የስራ ዕድሎችን በመፍጠር ገቢዋን ለማሳደግ ከማለሟም ባሻገር የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለሃገራዊ ምጣኔ ሃብት ዕድገት እያበረከተ የሚገኘውን የ5 በመቶ አስተዋፅኦ ወደ 22 በመቶ ለማሳደግ አስባለች። አሁን በተግባር ላይ የሚገኙት ማይክል ኮርስ፣ ኤች ኤንድ ኤም፣ ችልድረንስ ፕሌስ እንዲሁም ግዙፉ ፒቪኤች የተሰኙት አለም አቀፍ የልብስ ብራንዶች ዘርፉን የማሳደግ ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም ፅሁፉ በሃተታው አካቷል።

በጥንት ታሪኳም ኢትዮጵያ ሰማይ ጥግ የደረሰ ታሪክ አላት። ዘመን ተሻጋሪ ታሪኮች ካሳለፉ ጥቂት የአለማችን ሃገራት ተርታም ተሰልፋለች። ጠንካራ ታሪኳም ከአለት በጠነከረ ሁኔታ በተለያዩ ጥንታዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ድርሳናት ላይ ተከትበው ይገኛሉ። የራሷ የሆነ ፊደሏም ከአለም በጥንታዊነት ከሚነሱት አንዱ መገለጫዋ ነው። የራሷ የዘመን አቆጣጠር ቀመርን የምትከተለውና በአንድ ወቅት ስሟ የመላው አፍሪካ መጠሪያ እንደነበር እማኝነቱን በመረጃ ያስደገፈው ጋዜጠኛው  ለአውሮፓውያን ስልጣኔ መንገድ ለጠረገው የግብፅ ስልጣኔ ጥንታዊው የኢትዮጵያ ስልጣኔ አበርክቶው የገዘፈ እንደሆነም አስቀምጧል።

በመካከለኛው ዘመን እንደ አበባ ፈክተው ከወጡት እና እስካሁንም ከቀጠሉት ታላላቅ መንግስታት መካከል ኢትዮጵያ በከፍታ ልትነሳ የምትችል ሃገር ናት። በተጠቀሰው ዘመን ከነበሩት የማሊዋ ማንሳ ሙሳ እንዲሁም የታላቋ ዚምባቡዌ ታሪኮች በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች ሳቢያ ሊከስሙ ቢችሉም የጣሊያን ቅኝ ገዥን ሃይል ድባቅ በመቱት ልጆቿ ምክንያት ከአፍሪካ በቅኝ ያልተያዘችው ብቸኛዋ ሃገረ ኢትዮጵያ የጥንተ ታሪኳን እንደጠበቀች አሁንም መቀጠሏን ኦቲየኖ አፅንኦት ሰጥቶታል።

በስም የገዘፉት አለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን ስለ ኢትዮጵያ አዎንታ አዘል ሰፋ ያሉ ዘገባዎቻቸውን እያሰራጩ ይገኛሉ። ብሩኪንግስ የተሰኘው ተቋምም ከነዚህ ሊጠቀስ የሚችል ነው። ከላይ ከቀረበው መረጃ በተጨማሪም ሌላ ኢትዮጵያ የምትነሳበት ጉዳይ እንዳለም አመልክቷል። እሱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሃገር ውስጥም ሆነ በቀጣናው ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ይሰፍን ዘንድ እየተጫወቱት ያለውን በጎ ሚናን አንስቷል። በሃገር ውስጥ ለአመታት በእስር የቆዩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ከመፍታት በዘለለ ለሁለት አስርተ አመታት የቆየውን የኤርትራና ኢትዮጵያ ቅያሜ ወደ እርቅ እንዲመጣ በማድረጉ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰፊውን ድርሻ እንደሚወስዱም መረጃው አስቀምጧል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተጨማሪም የሶማሊያውን ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ፎርማጆ ወደ ናይሮቢ እንዲያቀኑ በማድረግ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ያላቸውን ቁርሾ እንዲፈቱ አገናኝቶ የማወያየት ቅዱስ ተግባርንም ፈፅመዋል።

በሌላም በኩል ባለፈው ግንቦት ነበር ኢትዮጵያ ከመላው አፍሪካ ለሚመጡ ዜጎች የመዳረሻ ቪዛ ብቻ በመጠቀም ወደ ሃገሯ እንዲገቡ የጋበዘችው ያለው የብሩኪንግስ መረጃ የአፍሪካን አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን በምክር ቤት በማፅደቅ 21ኛዋ ሃገር ልትሆን እንደቻለችም አስረግጧል።  

ከላይ የተጠቀሱት አስረጂዎች ስለ ኢትዮጵያ ለመመስከር የሚረዱ ከብዙ በጥቂቱ የተወሰዱ መረጃዎች መሆናቸውን የሚጠቅሰው ኬንያዊው ጋዜጠኛ ማቲው ኦቶየኖ ሃገሪቷን በቅርቡ ከደረሰው አደጋ ጋር ብቻ እያነሱ ሌላ የሚነገር ጉዳይ እንደሌላት አድርገው አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ታዳሚያቸውን ለማሳመን የሚያደርጉት ጥረት ትዝብት ላይ ሊጥላቸው እንደሚችል አፅንኦት ሰጥቶታል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚዋ የምጣኔ ሃብት እምቅ ሃይል ያላት ሀገር እንደሆነች የምታሳይበት ጊዜ ላይ ናት፤ የህዝብ ቁጥር ዕድገቷም በአለም በጣም ተፈላጊዋ ሃገር ያደርጋታል፤ ጥንተ ታሪኳም ሳይበረዝና ሳይከለስ እንዲሁ እንዳለ ይነገርላታል፤ ሲልም ጋዜጠኛው ሃሳቡን አጠናክሮ ቋጭቷል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም