በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ22 ሺህ በላይ የእጣንና ሙጫ ዛፍ ችግኝ ለመትከል እየተሰራ ነው

69
መተማ ግንቦት 24/2010 በምዕራብ ጎንደር ዞን የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከ22 ሺህ በላይ የእጣንና ሙጫ ዛፍ ችግኝ ለመትከል እየተሰራ መሆኑን በዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ አስታወቀ። የዞኑ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ አድጎ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት በመተማ፣ ቋራና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች የሚተከል ከ22 ሺህ በላይ የእጣንና ሙጫ ችግኝ ተዘጋጅቷል፡፡ የተዘጋጀው ችግኝ ከስድስት ሄክታር በላይ መሬት እንደሚሸፍንም አመልክተዋል፡፡ አቶ ሀብታሙ እንዳሉት፣ ችግኝ ተከላ ሥራው የሚካሄደው በየወረዳዎች በወጣቶች በተቋቋሙ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ቱሪዝም የሕብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ነው፡፡ ሕብረት ሥራ ማህበራቱ ከስድስት ሺህ በላይ አባላት እንዳላቸውም ተናግረዋል። ዞኑ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት እንዳለው የገለጹት አቶ አብታሙ ይህን ሀብት ያለአግባብ መጠቀም ከመከላከል ባለፈ መጠኑን ከፍ በማድረግ ወጣቶች ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መስራት ያስፈልጋል  ብለዋል፡፡ በመተማ ወረዳ ሌንጫ ቀበሌ በዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ቱሪዝም የተደራጀ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት በየነ ውቤ በበኩሉ " የእጣንና ሙጫ ዛፍ የእኛንና የቤተሰባችንን ሕይወት ለማሻሻል እያገዘ ነው" ብሏል። በመሆኑም ዛፎቹን ከመንከባከብና ከመጠበቅ ባለፈ ተጨማሪ ችግኝ በመትከል የማስፋፋት ሥራ ለማከናወን መዘጋጀታቸውን አመልክቷል። በሕብረት ሥራ ማህበሩ 166 አባላት መኖራቸውንና እያንዳንዳቸው በትንሹ ሦስትና ከእዚያ በላይ ችግኞችን ተክለው ለመንከባከብ ዕቅድ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡ "በአሁኑ ወቅት እየተጠቀምንባቸው ያሉትን የእጣንና ሙጫ ዛፎች ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ በእርጅና ምክንያት ምርት የማይሰጡ ዛፎችንና የደረቁትን በአዲስ መተካት አለብን" ያለው ደግሞ በዳስ ጉንዶ ቀበሌ የሚገኘው ሕብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት አበራ አድማሴ ነው፡፡ በሕብረት ሥራ ማህበራቱ የተቋቋመው ቴዎድሮስ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ቱሪዝም እድገት የኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ አያሌው በበኩላቸው ዩኑየኑ የእጣንና ሙጫ ዛፍ ችግኞችን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ዩኒየኑ ከ2006 እስከ 2009 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ለአባላቱ ማከፋፈሉንም አያይዘው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም