በባህርዳር ከተማ የእሳት አደጋ የንብረት ውደመት አደረሰ

63

ባህርዳር መጋቢት 20/2011 በባህርዳር ከተማ ግሽአባይ ክፍለ ከተማ ዛሬ ሌሊት ስምንት ሰዓት አካባቢ የተነሳው  የእሳት አደጋ ዘጠኝ የንግድ ሱቆች ማውደሙን  ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማው የሁለተኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ጽህፈት ቤት እንደገለጸው በቃጠሎው የወደመው ንብረትነቱ  ሃሙአ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሆነና ለገበያ ማዕከል የተገነቡ ሱቆች ናቸው።

በማዕከሉ ተከራይተው በምግብ ቤት፣ በሸቀጣሸቀጥና ሌሎች የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ሲሰሩ የነበሩ የዘጠኝ ግለሰቦች ንብረት መውደሙን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ብርሃን ስልጣን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት የፀጥታ አካላት፣ የአካባቢው ህብረተሰብና የባህርዳር እሳትና አደጋ መከላከል በጋራ ባደረጉት ጥረት እሳቱ ወደ ሌላ አካባቢ ሳይዛመት ከንጋቱ 11 ሰዓት አካባቢ በቁጥጥር ስር ውሏል።

የቃጠሎውን መነሻ ምክንያትና የወደመውን ንብረት ግምት ለማወቅ ምርመራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም