'አዲስ አበባ የኔ እንጂ ያንተ አይደለም' ከሚል የቆየ የተቃርኖ ትርክት በመውጣት ከተማዋን በጋራ ማልማት አለብን - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

138

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2011 " አዲስ አበባ የኔ እንጂ ያንተ አይደለም' ከሚል የቆየ የተቃርኖ ትርክት ወጥተን ከተማዋን በጋራ ማልማት አለብን" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሳቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባን በሚመለከት በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሱ የሃሰት ፕሮፓጋንዳዎች ሊቆሙ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ ለሚገኙ የአገር ውስጥና የውጭ የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ዛሬ በሰጡት መግለጫ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ አዲስ አበባ ያስቆጠረችውን ዘመን ያህል ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነ አገልግሎቶችን እየሰጠች አይደለም።

"በመሆኑም ለዚህች ከተማ የሚበጀው ጎራ ለይቶ 'የእኔ ናት ያንተ አይደለችም'  እያሉ መባላት ሳይሆን እንዴት በጋራ እናልማት የሚለው ጥያቄ ነው" ብለዋል።

ለዚህም መንግስት 'ሸገርን የማስዋብ' ፕሮጀክት ነድፎ ከተማዋን ውብ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

'በአዲስ አበባ መታወቂያ እየታደለ ነው' የሚለው ሃሳብ በስፋት መነጋገሪያ እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ከክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚዎች ጋር ባደረኩት ግምገማ ድርጊቱ እንዳልተፈጸመ አረጋግጫለሁ" ብለዋል።

አሁን ያለው የአዲስ አበባ የስነ ህዝብ ስርጭት (ዴሞግራፊ) ከመቶ በላይ አመታት የወሰደ ድምር ውጤት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ማንም ተነስቶ የአዲስ አበባን ስነ ህዝብ ስርጭት ላስተካክል ቢል ተራራን የመግፋት ያህል የማይቻለው ተግባር መሆኑን ጠቁመው፤ ጉዳዩን በሚመለከት በማህበራዊ ሚዲያ በሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎች ዜጎች እንዳይደናገጡ መክረዋል።

በመሰል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም