በክልሉ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በፍጥነት ወደ ገቢ ማስገኛ ምንጭ መቀየር አለበት--- ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል

109

መቀሌ መጋቢት 19/2011 በትግራይ ክልል በህዝቡ ነጻ ጉልበት እየተሰራ ያለውን የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በፍጥነት ወደ ገቢ ማስገኛ ምንጭ መቀየር እንዳለበት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል አሳሰቡ፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የአጽቢ ወንብርታና የክልተ አውላአሎ ወረዳዎች በዘመቻ እየተካሄደ ያለውን የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ጎብኝተዋል፡፡

በዚህ ወቅት ዶክተር ደብረፅዮን  በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ ሐየሎምና ቃል አሚን ቀበሌ ገበሬ ማህበራት በመካሄድ ላይ ያለውን የአፈርና ውሀ ጥበቃ ዘመቻ ውጤታማ እንደሆኑ በመስክ መመልከታቸውን ተናግራዋል፡፡

"ህዝቡ የተራቆቱ አካባቢዎችን ለማልማት እያደረገ ያለውን ርብርብ ውጤታማ ቢሆንም በፍጥነት የገቢ ማስገኛ ምንጭ እንዲሆን በማድረግ በኩል ብዙ ስራ ይቀረናል" ብለዋል፡፡

በክልሉ ያለፉት ዓመታትን ጨምሮ አሁንም  እየተሰሩ ያሉት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ለም አፈር በጎርፍ ከመሸርሸር  መከላከል እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

በዚህም  ስራው ከተካሄደባቸው ተፋሰሶች  ምንጮችን በመጎልበታቸው የውሀ ጉድጓዶችን በመጠቀም በመስኖ የመልማት ጅምሮች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

ጅማሮ ቢሆንም ከእንስሳትና ሰው ንኪኪ ነጻ የሆኑ ከፍታማ  ቦታዎች ለእንስሳት ሃብት መኖ እና በንብ ማነብ ወጣቶች እንዲሰማሩ አድርጓል፡፡

"ሰላማችን በማስጠበቅ ልማታችን የማፋጠን ስራዎችን በተቀናጀ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል " ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ  የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በፍጥነት ወደ ገቢ ማስገኛ ምንጭ መቀየር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ከ20 ዓመታት በፊት በክልሉ በመስኖ ይለማ የነበረውን ከ4ሺህ ሄክታር መሬት እንደማይበልጥ  የተናገሩት ደግሞ  የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ክፍሎም አባዲ ናቸው፡፡

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት ስራዎች  አሁን ላይ 48ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት መቻሉ  የአከባቢ ጥበቃ ስራ ውጤት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

"የአፈርና ውሀ ጥበቃ የተካሄደባቸው አካባቢዎች በሙሉ ወደ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በመቀየር በኩል ብዙ ይቀረናል" ብለዋል፡፡

በተለይም ወጣት አርሶ አደሮች ቀጣይነት ያለው ስራ በማከናወን  ከድህነት እንዲላቀቁ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ ሓየሎም ቀበሌ  በአፈርና ወሃ ጥበቃ ዘመቻ ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል ዲያቆን ካህሳይ አባይ እንደገለጹት ላለፉት   20 ዓመታት በአካባቢያቸው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ አከናውነዋል፡፡

በዚህ ተጉድቶ የነበረው አካባቢያቸው  በማገገሙ  ሁለት ጥማድ መሬታቸው በዓመት ሁለት ጊዜ የተለያዩ አትክልቶችን በመስኖ በማልማት ወደ ባለሀብት መሸጋገራቸውን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ አንድ ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ሁለት ቤቶች በሀይቅ መሳሀልና ውቅሮ ከተሞች ከማስገንባታቸው በተጨማሪ አንድ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ባለቤት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በአጽቢ ወንብርታና የክልተ አውላአሎ ወረዳዎች  ለሀያ ቀናት ያህል የሚካሄደውን  ስራ ዛሬ የጎበኙት በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች ጨምሮ ከ200 በላይ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም