የአማራ ክልላዊ መንግስት ለ4 ሺህ 270 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

115

ባህርዳር መጋቢት 19/2011 የአማራ ክልላዊ  መንግስት ለአራት ሺህ 270 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

በጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግ ማስፈፀም ዘርፍ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ሙሉጌታ አበራ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ከክልሉ ማረሚያ ቤቶች ይቅርታ ከተደረገላቸው መካከል 65ቱ  ሴቶች ናቸው፡፡

በተሰጠው ይቅርታም ከዝቅተኛ እስከ ዕድሜ ልክ ፍርደኛ የሆኑ ታራሚዎች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

ይቅርታ የተደረገላቸው ሰዎች  በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ባመጡት የባህሪ ለውጥ ጉዳያቸው በይቅርታ ቦርድ ታይቶ ለክልሉ ካቢኔ ከቀረበ በኋላ  ውሳኔ በማግኘቱ የይቅርታው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስታውቀዋል።

ተጠቃሚ የሆኑትም የክልሉ መንግስት በዓመት ሁለት ጊዜ ይቅርታ እንዲሰጥ በወሰነው መሰረት የተፈፀመ መሆኑንም አመልክተዋል።

እንደ ኤች አይቪ፣ ስኳር፣ ካንሰርና በመሳሰሉት በማይድኑ በሽታዎች የተያዙ፣ በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ታመው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው የነበሩ ታራሚዎች የይቅርታው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።

ከህፃናት ጋር የታሰሩ እናቶች፣ የዩኒቨርሲቲ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ዕርቅን በማይጠይቁ ጉዳዮች የይቅርታው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉም ተመልክቷል፡፡

የይቅርታው ተጠቃሚ ከሆኑት መካከልም 13 የዕድሜ ልክ ፍርደኞች እና  38 በዕድሜ የገፉ እንደሚገኙበትም ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ጠቅሰዋል።

የይቅርታው ተጠቃሚ የህግ ታራሚዎችም ከዛሬ ጀምሮ ከየማረሚያ ቤቶች እንዲለቀቁ መደረጉን  አመልክተው  ህብረተሰቡ ተገቢውን  ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም መልዕክታቸወን አስተላልፈዋል።

በሙስና ወንጀል፣ በአስገድዶ መድፈርና በመሳሰሉት ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በህግ ጥላ ስር የሚገኙትን ይቅርታው እንደማይመለከትም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም