በመብራት መጥፋትና መቆራረጥ ስራችንን በአግባቡ መስራት አልቻልንም-በደብረብርሃን ከተማ የተደራጁ ወጣቶችና ባለሀብቶች

69
ደብረ ብርሃን ግንቦት 24/2010 በመብራት መጥፋትና መቆራረጥ ምክንያት ስራቸውን በአግባቡ መስራት እንዳልቻሉ በደብረብርሃን ከተማ ተደራጅተው በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶችና ባለሀብቶች ገለፁ፡፡ በምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን  ደብረብርሃን ዲስትሪክት በበኩሉ በከተማው ያሉ ትራንስፎርመሮች ያረጁ በመሆናቸው እንዲቀየሩ ለአስተዳደሩ ብናሳውቅም መልስ በማጣታችን ችግሩን መቅረፍ አልቻልንም ብሏል፡፡ በደብረብርሃን ከተማ 07 ቀበሌ አማን፣ አስራርና ጓደኞቹ ብሎኬት አምራች ህብረት ሽርክና ማህበር አራት ሆነው ከተደራጁ ወጣቶች መካከል ወጣት አስራር ጀማል በሰጠው አስተያየት በ60 ሺህ ብር ካፒታል ወደ ስራ ቢገቡም በመብራት መጥፋትና መቆራረጥ ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳልቻሉ ገልጿል፡፡ በቀን ከ600 እስከ 800 ብሎኬት በማምረት የጀመሩት ስራ በመብራት መቆራረጥ ሳቢያ ከ120 በታች ለማምረት መገደዳቸውን አስታውቋል፡፡ ብሎኬት ለማምረት ያዘጋጁት አሸዋና ሲሚንቶም ወደ ድንጋይነት በመቀየሩ ለኪሳራም እየተዳረጉ መሆኑን ገልጿል፡፡ ስራውን በጀመሩበት ወቅት በቀን 8ሺህ ብር ያገኙ እንደነበር ያስታወሰው  ወጣት አስራር በመብራት መቆራረጥ ሳቢያ ገቢያቸው ወደ 1 ሺህ 200 ብር ዝቅ በማለቱ የልፋታችንን አጥተናል ብሏል፡፡ ከመስከረም፣ መቅደስና ጓደኞቿ ብሎኬት ማምረት ህብረት ስራ ሽርክና ማህበር ወጣት መስከረም ምንዳ ''በቀን ከ4 ጊዜ በላይ ስለሚጠፋ ከምንሰራው የማንሰራበት ሰዓት ይበዛል'' ብላለች፡፡ ሀይሉም ደካማ በመሆኑ ማሽኑን ለማንቀሳቀስ ስለሚከብደው የሚፈለገውን ያህል እያመረቱ እንዳልሆነና ለኪሳራ እየተዳረጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ''አሸዋና ሲሚንቶውን ከተዋሃደ በኋላ መብራት ከአንድ ሰዓት በላይ ጠፍቶ ከቆየ ስለሚደርቅ ለኪሳራም እየተዳረግን ነው'' ብላለች፡፡ የጁኒፐር ጠርሙስ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ሙሉጌታ በበኩላቸው ስራቸውን በአግባቡ መስራት ባለመቻላቸው ከዓመት በፊት አዲስ ትራንስፎርመር እንዲገባላቸው 3 ሚሊዮን ብር ቢከፍሉም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ስራውን በጀኔሬተር ለመስራት ቢገደዱም ነዳጅ በመጨመሩ ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ የምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን  የደብረብርሃን ዲስትሪክት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ቸርነት በበኩላቸው ''ከተማው በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በመምጣቱና ትራንስፎርመሮችም በማርጀታቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ከህዝቡ ጋር መጣጣም አልቻለም'' ብለዋል፡፡ ያረጁ ትራንስፈርመሮች ከአቅማቸው በላይ በማስተናገዳቸውም በተደጋጋሚ በሚከሰት የመብራት መቋረጥ በደንበኞች ላይ መጉላላት እየደረሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ግን የዲስትሪክቱ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን  አስተዳደሩ የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ ''በቻልነው አቅም ግን ከሁለት ዓመት በፊት የተቃጠሉ ሦስት ትራንሰፎርመሮችን በቅርቡ በመቀየር ችግሩን ለማቃለል ሞክረናል'' ብለዋል፡፡ በከተማው ባሉ ቀበሌዎች ከስድስት ኪሎ ሜትር በላይ የተተከሉ ያረጁ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን በመቀየር የመብራት መቆራረጥና መጥፋትን ችግርን መቀነሳቸውን ገልጸዋል፡፡ የደብረብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው ''ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ቀጣይ ከሌሎች በጀቶች ቀንሰን ለትራንስፈርመር መግዣ እንመድባለን'' ብለዋል፡፡ ''እስከዚያው ግን በቀላሉ መስተካከል የሚችሉትን ባለሙያዎች እያስተካከሉ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል'' ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም