የመንገድ ትራፊክ ደንብ የሚተላለፉ እግረኞችን የሚያስተምር ቅጣት ተግባራዊ ሊደረግ ነው- የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን

417

አዲስ አበባ  መጋቢት 19/2011የእግረኞች የመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ በሙከራ ደረጃ በተመረጡ የሀገሪቱ ከተሞች ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።

ደንቡን በአዲስ አበባ በተወሰኑ ቦታዎች በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ መተግበር እንደሚጀመር የገለፀው ደግሞ የከተማዋ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ነው።

እግረኞች የመንገድ ላይ የትራፊክ ደንብን አክብረው የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ በህግ መደንገግ በማስፈለጉ የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/2009 በሚኒስቴሮች ምክር ቤት እንዲሻሻል ተወስኗል።

በተሻሻለው ደንብ ቁጥር 395/2009 መሰረትም በእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ላይ የተጣሉትን ቅጣቶች ለማስፈጸምም የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን መመሪያ ማዘጋጀቱ ይታወቃል።

የመመሪያው ዓላማ በመንገድ ላይ ደህንነቱ የተጠበቀ የትራፊክ እንቅስቃሴን ለማረጋገጥና የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክን ለመቆጣጠር ተሻሽሎ በወጣው ደንብ መሰረት የእግረኞችን የቅጣት አፈፃጸም ድንጋጌ በግልፅና ወጥ በሆነ መንገድ ተፈፃሚ ማድረግ ነው።

በባለስልጣኑ የመንገድ ደህንነት ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክተር አቶ ዮሃንስ ለማ ለኢዜአ እንዳሉት የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ሊሰራባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል የእግረኞች የትራፊክ አጠቃቀም ዋነኛው ነው።

በትራፊክ አደጋ ከሚደርሱ ጉዳቶች ከፍተኛው ተጎጂም እግረኞች መሆናቸውን የገለፁት ዳይሬክተሩ በአዲስ አበባ የትራፊክ አደጋዎች ካደረሱት ጉዳቶች 80 በመቶ ያህሉ በእግረኛ ላይ የደረሱ መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

እናም እግረኞችን ከትራፊክ አደጋ ለመጠበቅ የሚያግዘውን ደንብ እግረኞች በስርዓት እንዲጓዙና ይህን የማያደርጉትን ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል።

ደንቡን በሙከራ ደረጃ በተመረጡ አካባቢዎች እንዲተገብሩ ለማስቻልም ለሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ባለስልጣኑ መመሪያ መስጠቱንም አብራርተዋል።

አሁንም በመንገድ አጠቃቀም የተሻለ ልምድ ያላቸው የአዊ ዞን የመሳሰሉ አካባቢዎች በሁሉም ክልል እንዳሉ ተናግረው ደንቡ ተግባራዊ የሚደረገው ከነዚህ ቦታዎች ውጪ ባሉ ቦታዎች መሆኑንም ገልፀዋል።

ደንቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው ሙከራ ያመጣው ውጤት ተገምግሞ ሙሉ በሙሉ የሚተገበር እንደሚሆንም ተናግረዋል።                      

የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ታመነ በሌ በበኩላቸው ደንቡን ለመተግበር ካለፈው ዓመት ጀምሮ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ኤጀንሲው ማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራውን እያከናወነ መሆኑንና በቀጣይም ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች መንገዶችን ለእግረኞች የተመቸ ለማድረግ የእግረኛ ማቋረጫዎች ቀለም ቅብ፣ ምልክትና ማመላከቻዎችን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗልም ብለዋል።

ደንቡን በቀለበት መንገዶች፣ ዋና ዋና መንገዶችና እግረኞች ያለአግባብ በሚዘሉባቸው ቦታዎች መተግበር እንደሚጀመርም አብራርተዋል።

ደንቡ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግና የግንዛቤ ማስጨበጫና መንገዶችን ለእግረኛ ምቹ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የተሻሻለው የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/2009” የመንገድ ተጠቃሚዎች ሁሉ የመንገድ ማመላከቻ እና ምልክቶችን እንዲሁም ሌሎች የትራፊክ ፍሰቱን ቀልጣፋ ለማድረግ የወጡ ህጎችን በማክበር የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን ደህንነት እንዲጠብቁ የሚያስገድድ ሕግ ሲሆን የወጡ ሕጎችን ጥሰው በተገኙ የመንገድ ተጠቃሚዎች ላይ የእርከን ቅጣት ይጥልባቸዋል።

ደንቡ ለጥፋቶች እንደየክብደታቸው 40 ብር እና 80 ብር በቅጣት እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ሲሆን በደንቡ ከተጠቀሱት ጥፋቶች አንዱን ፈፅሞ ክፍያ መፈጸም ያልቻለ ወይም ያልፈለገ ማንኛውም ሰው ተመጣጣኝ የሆነ ማህበራዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም