ሞዴል የማህበረሰብ መድሃኒት ቤት መመሪያ ከ25 በመቶ በላይ ትርፍ የሚፈልጉ መድሃኒት ቤቶችን እንደሚቆጣጠር ተገለጸ

177

አዲስአበባ መጋቢት18/2011 ሞዴል የማህበረሰብ መድሃኒት ቤት መመሪያ መንግሰት ያወጣውን ከሃያአምስት በመቶ በላይ ትርፍ የሚፈልጉ መድሃኒት ቤቶችን እንደሚቆጣጠር ተገለጸ።

ዛሬ የጸደቀው ሞዴል የማህበረሰብ መድሃኒት ቤት መመሪያ ከ0.6 እስከ 25 በመቶ ብቻ ትርፍን ታሳቢ አድርገው መድሃኒቶችን ለህብረተሰቡ እንዲያቀርቡ የሚያስችል መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የህክምና አገልግሎት ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ሰማን ገልጸዋል።

መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ በታሰበበት ወቅት በተደረገ ጥናትም አንዳንድ የግል መድሃኒት ቤቶች ከ400 ፐርሰንት በላይ ትርፍ በማግኘት ሲሰሩ እንደነበር ተገልጿል።

ዛሬ የጸደቀው መመሪያ ዓላማም ህብረተሰቡ ፈዋሽ መድሃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት የሚችልበት ምቹ አሰራር መዘርጋት ነው።

የግል መድሃኒት ቤቶች በበኩላቸው ያቀረቡት ምክንያት መንግስት ለመንግሰት መድሃኒት ቤቶችና ለግል መድሃኒት ቤቶች የሚሰጠው ምልከታ እኩል አለመሆኑን እና  የውጭ ምንዛሬ የማግኘት እድልም አናሳ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ያዕቆብ አክለውም የተለየ አተያይ ካለ ታይቶ የሚስተካካል ይሆናል ብለዋል።

መድሃኒት ቤት የሌለባቸው ቦታዎች እና የጋራ መኖሪያ ቤቶችም ተለይተው  በቀጣይ ሶስት ወራት ውስጥ ተቋሙ አምሳ መድሃኒት ቤቶችን ለመክፈት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ተናግረዋል።

በተያያዘም ኢትዮጵያ ከምታስገባው መድሃኒት በየአመቱ 15 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚገመቱ መድሃኒቶች ለብልሽት እንደሚዳረጉ በሚኒስቴሩ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ረጋሳ ባይሳ ተናግረዋል።

ለዚህም ምክንያቱ ከ75 በመቶ በላይ መድሃኒቶች ከውጭ ስለሚገቡና በጉዞ ወቅት የሚወስደው ጊዜ ረጅም መሆን እንዲሁም ከመድሃኒት ስርጭቶች ጋር ያለው ተግባቦት አናሳ መሆኑን ይናገራሉ።

ችግሩንም ለመፍታት ኢትዮጵያ ውስጥ መድሃኒት ፋብሪካዎችን ለማስፋፋት መታሰቡንና የመድሃኒት ስርጭቱን በማዘመን መድሃኒት ሲገባ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኤሊክትሮኒክስ በሆነ መንገድ የሚያይበትና የሚከፋፈሉበት አሰራር ለመዘርጋት መመሪያው እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በመሆኑም መድሃኒት ቤቶች በዚህ መመሪያ መሰረት ለመስራት ፈቃደኞች መሆናቸውንም አቶ ባይሳ ተናግረዋል።

በምሽት የሚሰሩ መድሃኒት ቤቶችም ዝርዝር ወጥቶላቸው ህብረተሰቡን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገለግሉበትን ሂደትም ጭምር ዝግጅት መጠናቀቁን እና በመገናኛ ብዙሃንም ይፋ እንደሚደረጉ ገልጸዋል።

 ከዚህ መመሪያ ውጭ የሚሰሩ መድሃኒት ቤቶችን ህብረተሰቡ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲያደርጉም ኣሳስበዋል።

የዚህ ዓይነቱን መመሪያ የተገበሩ እንደነ አሜሪካ ያሉ አገሮች እየተጠቀሙበት ያለ መሆኑንና የተነሱ ችግሮችን ሁሉ እየፈቱበት መሆኑንም አቶ ባይሳ አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም