በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ክልል ውስጥ የተነሳው ሰደድ እሳት በቁጥጥር ስር ዋለ

88

ጎባ መጋቢት 18/2011 በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ክልል ውስጥ የተነሳውን ሰደድ የእሳት ቃጠሎ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር መቻሉን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ  አቶ አስቻለው ጋሻው ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ጎባና ዲንሾ ወረዳዎች ውስጥ ተከስቶ የነበረውን ሰደድ  የእሳት ቃጠሎ መቆጣጠር የተቻለው ትናንት ማምሻውን ነው፡፡

በፓርኩ ክልል በቀላሉና በፍጥነት በሚቀጣጠሉ አስታ የተባሉ  የዛፍ ዝርያዎች መሸፈኑ እሳቱ በቀላሉ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበረም አስታውሷል፡፡

እሳቱ ያደረሰውን ጉዳት ለጊዜው ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው  ቃጠሎው የተከሰተባቸው አካባቢዎች  የነበሩ የአስታ ዛፍ ዝርያዎችና  ሌሎች ብዝሐ ህይወት ላይ ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል፡፡

አቶ አስቻለው እንዳመለከቱት የእሳት ቃጠሎው ለጊዜው በህብረተሰቡ ተሳትፎና በአካባቢው ላይ በሚታየው ደመናማና ዝናባማ የአየር ንብረት የጠፋ ቢሆነም በአፈር ውስጥ ቆይቶ ዳግም የመነሳት ባህሪ  ስላለው ተከታታይ ክትትልና ጥንቃቄ እንደሚሻ ነው፡፡

የሰደድ እሳቱን ለመቆጣጠር ከተደረገው ጥረት በተጓዳኝ እሳቱን በማቀጣጠል የተጠረጠሩ 17 ግለሰቦችን ፖሊስ በመያዝ ምርመራ እያደረገባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እሳቱ ወደ ዋናው የፓርኩ የደን አካል እንዳይዛመት የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ፣ የፀጥታ አካላት፣ የጎባና ሮቤ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች  ርብርብር በማድረግ ላበረኩቱት አስተዋጽኦ ኃላፊው አመስግነዋል፡፡

በፓርኩ ብዝሐ ህይወት ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ የሚገኘውን ሰው ሰራሽ አደጋ ለመከላከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ ህግን በሚተላለፉ ሰዎች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ እንዲጠናከር በየደረጃው ከሚገኙ የፍትህ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራበት መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

ህብረተሰቡም የፓርኩን ህልውና የሚፈታተኑ ችግሮችን ለመፍታት የድርሻው እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ 

በእሳት ማጥፋቱ ሂደት ላይ ከተሳተፉ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ኢብሳ ከድር አንዱ ነው፡፡

ተማሪው በሰጠው አስተያየትም ህብረተሰቡ  ከፓርኩ የሚገኘውን ጥቅም እንዲጋራና ባለቤትነቱን እንዲያጎለብት በማድረግ በተፈጥሮ ሀብቱ  ላይ እየደረሰ ያለው  ጫና ለመቀነስ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አመልክቷል፡፡ 

መንግስትና በየደረጃው የሚገኙ በፓርኩ ላይ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ለፓርኩ ልማትና ጥበቃ የሰጡት ትኩረት አነስተኛ መሆኑን በሀብቱ ላይ እየደረሰ ያሉው ጉዳት ማሳያ መሆኑን የገለጹት ደግሞ እሳቱን ለመቆጣጠር ከሮቤ ከተማ የተሳተፉት  አቶ አማረ ቢፍቱ ናቸው፡፡

አቶ አመረ እንዳሉት መንግስት በደኑ አካባቢ በየጊዜው እሳት ሲነሳ ተከታትሎ ከማጥፋት ይልቅ፤ በህገ ወጦች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ሊያጠናክር ይገባል።

በባሌ ተራሮች ብሔረዊ ፓርክ ክልል ውስጥ ማንነታቻው ባልታወቁ ሰዎች የሰደድ እሳት መከሰቱን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል፡፡

ባለፈው ወርም ለስድስት ቀናት የቆየ  የሰደድ እሳት በፓርኩ ብዝሐ ህይወት ላይ ጉዳት አድርሶ ነበር፡፡

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም /ዩኔስኮ/ በጊዜያዊ ቅርስነት የተመዘገበው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተለያዩ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና  አእዋፍ መገኛ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም