በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር የመቀሌን ኢንዱስትሪ ፓርክ ጎበኙ

105

መቀሌ መጋቢት 17/2011 የፓኪስታን ባለሃብቶች በትግራይ ክልል ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር አስግሃር ዓሊ ገለጹ።

አምባሳደሩ የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ዛሬ  ጎብኝተዋል፤  ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋር በልማት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ወቅት አምባሳደሩ እንዳሉት  ከመካ የተሰደዱት ሙስሊሞች በትግራይ ክልል አልነጂሺ ፍቅርና ክብር በመስጠት እንዲኖሩ መደረጉ  በፓኪስታኒያዊያን ዘንድ የማይረሳ ነው ።

" እኔ ወደዚህ ክልል ስመጣ ወደ ቤቴ እንደገባሁ ነው የምቆጥረው " ያሉት አምባሳደሩ የሀገራቸው በጎ ፈቃደኞች በጤናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅኦ በማስፋት በሌሎች የልማት ዘርፎችም እንዲሳተፉ የበኩላቸው ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

የአልነጃሺ መስጊድ የሚገኝበት ወረዳ ከሀገራቸው ላሆ  ከሚባለው  ከተማ ጋር እህትማማችነት ለመፍጠር ጥረት እንደሚያድረጉም ነው የተናገሩት፡፡

በጨርቃጨርቅ፣ አልባሳትና ሌላም ልማት ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ የፓኪስታን ባለሃብቶች በብዛት  እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡

አምባሳደሩ ባለሃብቶቹ በተለይም የአልነጃሺ ታሪካዊ ስፍር በሚገኝበት አካባቢ በልማት ለመሳተፍ የተለየ ፍላጎት እንዳላቸው አስረድተዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው ባለሀብቶች አስተማማኝ ሰላም፣ ሰፊ የሰው ጉልበትና የስራ ባህል ባለው አካባቢ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ  ቢሰማሩ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

አልባሳር ኢንተርናሽናል የተባለው የፓኪስታኒያዊን  በጎ ፈቃደኞች ድርጅት አማካኝነት ነፃ የዓይን ህክምና በመስጠት በክልሉ ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡

በክልሉ ባለው ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ መሳተፍ ለሚፈልጉ የፓኪስታን  ባለሃብቶችን  በፀጋ በመቀበል አስፈላጊው ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ዶክተር ደብረፅዮን አስታውቀዋል፡፡

አምባሳደሩ በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለውን  ጨርቃ ጨርቅ የማምረት ስራ ሂደት የጎበኙ ሲሆን ፓርኩ ስላለበት አጠቃላይ ይዘትና  ለውጭ ባለሃብቶች ስላለው ምቹ ሁኔታ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡

በኢንቨስትመንት፣ በጤናና በቱሪዝም ዘርፍ ዙሪያም  ከዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጋር ተወያይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም