በኢትዮጵያ የልጅነት ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን በ2025 ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ስምምነት ተደረገ

50

አዲስ አበባ  መጋቢት 17/2011 በኢትዮጵያ ያለዕድሜ ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን በ2017ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት በትብብር እንደሚሰሩ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔና የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጹ።

ሁለቱ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ተግባራት በጋራ ለማከናወንም የመግባቢያ ሰነድ ዛሬ ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ መጋቢ ዘርይሁን ደጉ እንደተናገሩት፤ ከሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ጋር የተደረገው ስምምነት በአገር አቀፍ ደረጃ የልጅነት ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ማጥፋት ግብ አስቀምጧል።

ለስኬታማነቱ ጉባዔው በየቤተ እምነቱ ባሉ የኃይማኖት አባቶች አማካኝነት ሴት ልጅ መገረዝ እንደሌለባትና ያለ ዕድሜዋ ጋብቻ እንዳትፈጽም መከላከል ላይ እንዲያስተምሩ ይደረጋልም ብለዋል።

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ፀጋይ በበኩላቸው በሴቶች ዙሪያ በተለይ የልጅነት ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመቀነስ በሚኒስቴሩ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የኃይማኖት አባቶች በየቤተ እምነቱ ባላቸው አስተምህሮት በሚያከናውኗቸው ተግባራት ሰፋፊ ለውጦች የሚያስመዘግቡ በመሆናቸው የልጅነት ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመቀነስ በጋራ ለመስራት ሚኒስቴሩ ባለው ፍላጎት መሠረት የተደረገ ስምምነት እንደሆነም አብራርተዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ችግሩ በስፋት በሚታይባቸው በተላይም በአፋርና ሱማሌ ክልሎች ከዚህ በፊት በኃይማኖት አባቶችና በአገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በተከናወኑ ተግባራት ለውጥ ማምጣት እንደተቻለም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ  የልጅነት ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ተከላካይ ግብረ ኃይልም በሁሉም ክልሎች ተቋቁሞ በመስራት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በመግባቢያ የስምምነት ፊርማ ላይ ከሁሉም ክልሎች የመጡ የኃይማኖት አባቶች የተገኙ ሲሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን ዕርዳታ ድርጅትም በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ለወደፊቱም የልጅነት ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በጋራ እንደሚሰሩም ታውቋል።

ኢትዮጵያ በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም ባስተናገደችው የታዳጊ ሴቶች ብሄራዊ ጉባኤ ያለዕድሜ ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን እ.አ.አ በ2025 ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝና የበኩሏን ለማድረግ ቃል መግባቷ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም