የከርሰ ምድር ጎተራ

154

ሳሙኤል አያነው ከአርባ ምንጭ ኢዜአ---

በአሁኑ ጊዜ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ፣ ከህብረት ይልቅ ግለኝነት በሚንፀባረቅበት  ዘመን ላይ ድኩማሞዎች ግን አንድነታቸውን ያስተሳሰረውን የከርሰ ምድር ጎተራን የእኔ ሳይሆን የእኛ በሚል እስካሁን ጠብቀው  አኑረዋል ፡፡

”ዲኩማሞ ” ማለት በዲራሼ ወረዳ የሚገኙ አራት ብሔረሰቦች ማለትም ዲራሼ ፣ ኩስሜ ፣ ማሾሌና ሞስየ ምህጻረ ቃል ነዉ ፡፡

ከርሰ ምድር ጎተራዉ በእነዚህ ማህበረሰብ ስያሜ “ፖሎት” ይባላል ፡፡ ከስሙ ለመረዳት እንደሚቻለው አርሶ አደሮቹ በየቤታቸው እህል የሚያከማቹት በዚሁ የምድር ውስጥ ጎተራ ነው ፡፡

ማህበረሰቡ አዝመራ ከደረሰ በኋላ በደቦ እና በወንፈል በአንድነት  ምርቱን ሰብስበው ወደ ጎተራ በማስገባት ይታወቃሉ ። ይህ ሂደት ማህበረሰቡን በጠንካራ ማህበራዊ  ግንኙነት በማስተሳሰሩ ተዋደው ፣ ተቻችለውና ተከባብረው ለዘመናት ዘልቀዋል ፡፡

ምንም እንኳን  በብሔረሰብ ፣ በቋንቋ ፣ በታሪክ ፣ በቅርስ ፣ በስነ-ጥበብና በባህል የሚለያዩ ቢሆኑም በባህል እሴቶች ውስጥ አንድ ናቸው ፡፡

ለዛሬው ግን አንድነታቸውንና ን ያስተሳሰራቸውን ባህሪይ ለማስነበብ ሳይሆን “ፖሎት” ምንድነው? ለምን ይጠቅማል? የሚለውን ለማሳየት ፈልጌ ነው

 ፡፡  “ፖሎት”  የሚለውን ስም ወደ አማርኛ ሲተረጎም የከርሰ ምድር ጎተራ እንደ ማለት ነው  ፡፡ ፖሎት የአራቱም ብሔረሰቦች አገር በቀል ዕውቀት መሆኑን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባህል ተመራማሪ አቶ ፍሬው ተስፋዬ  ለመረዳት ችያለሁ ፡፡

ይህን ባህላዊ የከርሰ ምድር ጎተራ ማህበረሰቡ ከጥንት ጀምሮ የሚጠቀመው ቢሆንም የበለጠ ጥቅም ላይ የዋለዉ ግን ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ በኋላ ነበር ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በጣሊያን ወረራ ጊዜ በሌሎች አከባቢ የሚገኙ እህሎች በቦምብና በእሳት ቃጠሎ ሲወድሙ በደራሼ ወረዳ የሚገኘው እህል ግን ሳይጎዳ በመትረፉ ነው ፡፡

ከዚሁ የተነሳ እህል የተጎዳባቸውና ለምግብ እጥረት የተጋለጡ የጎረቤት ወረዳዎች እህል እስኪደርስ ድረስ ህይወታቸውን ያቆዩበት ጭምር በመሆኑ ልዩ ትውስታን ይፈጥራል ፡፡

ለአቶ ፍሬው ይህን አገር በቀል ዕውቀት ለሌላው አካባቢ ለማስተዋወቅ ለምን አልተሞከረም ብዬ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ “የከርሰ ምድር ጎተራን ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ከሸምበቆና ከቀርከሃ የሚሠራና  ባለ ሰባት ኖታ ድምጽ ያለው “ፊላ “የተሰኘ ድንቅ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ  እንዲሁም በባህላዊ ዘዴ የመሬትን ለምነት ለረዥም ጊዜ የሚያቆዩበት ልዩ የባህል ትሩፋት መኖሩን ጠቁመው ለማስተዋወቅ ደግሞ ፌስቲቫሎችን ከማዘጋጀት ባለፈ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል  ፡፡

የዲራሼ ወረዳ ልማት ማህበር ስራአስኪያጅ አቶ አወቀ ኪታንቦ እንደነገሩኝ ከሆነ “ፖሎት “የተሰኘው  የከርሰ ምድር ጎተራው  ከላይ ሾጠጥ ያለ ጥልቀቱ አስር ሜትርና ከዚያ በላይ እንዲሁም ስፋቱ አራት ሜትርና ከዚያ በላይ መሬት ውስጥ ተቆፍሮ የሚዘጋጅና ክዳን ያለው ሲሆን እህል የመያዝ አቅሙ እንደ አርሶ አደሮቹ ፍላጎት ሆኖ ከአንድ መቶ ኩንታል በላይ  ይደርሳል  ፡፡

“ፖሎት” ከተለያየ አደጋ ከመከላከሉም በላይ በድርቅና ረሃብ ጊዜ ተብሎ የሚቀመጠውን የቁጠባ እህል  ዘመናዊ የተባይ ማጥፊያ ኬሚካል ሳያስፈልገው እስከ አርባ ዓመት ድረስ እህል ሳይበላሽ ማቆየት ያስችላል ። ልጆቻቸው ጋብቻ በሚመሠረቱበት ጊዜ ተጋቢዎች ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ በጎተራው የሚገኘውን እህል ወላጆች በስጦታ የሚያበረከቱት ሌላኛው መገለጫቸው ነው  ፡፡

በከርሰ ምድር ጎተራ ውስጥ  በብዛት የሚቀመጡት የአገዳ እህሎችን  ማለትም በቆሎና  ማሽላ የመሳሰሉትን ነው  ፡፡ 

አዝመራውን  በደቦና በወንፈል ከወቁ በኋላ በቤት አቅራቢያ በተቆፈረው ጎተራ እንደሚከማች በወረዳው የአተያ ቀበሌ አርሶ አደር  ካርቶ ከበደ አጫውተውኛል ።ጎተራው በመሬት ውስጥ በመሆኑ ከቤተሰብ ባለፈ ማንም ሰው ሊያውቀው  አይችልም ፡፡

ጎተራው በቀዳዳው ልክ በተጠረበ ክብ ድንጋይ ተከድኖ አፈር የሚለብስ በመሆኑ ለሌባ  ምንም ዓይነት ፍንጭ አይሰጥም ፡፡ ሌባ ቢያገኝውም እንኳ ጎተራው በከባድ ሙቀት የታመቀ በመሆኑ በፍጹም አያስጠጋውም ፡፡ የጎተራው ባለቤትም ቢሆን እህል በሚያስፈልግበት ሰዓት የጎተራውን ክዳን ከከፈተ በኋላ እንዲናፈስ ከተደረገ በኋላ ነው ማውጣት የሚቻለው  ፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት በድርቅና በረሃብ ጊዜ እንጂ አዘውተረው የማይጠቀሙት በመሆኑ የአርሶ አደሩን የቁጠባ ባህል በእጅጉ ያግዛል ፡፡

ሰሞኑን የአካባቢውን ባህላዊ ትውፊቶች የሚተዋወቁበት ፌስቲቫል  በዲራሼ ወረዳ ጊዶሌ ከተማ ተዘጋጅቶ ነበር ። እኔም ከሙያዬ አንፃር በቦታው ተገኘሁና  የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ወክለው የመጡ አቶ ካሳሁን አያሌውን የማነጋገር እድል ገጠመኝ ።

የአካባቢው እምቅ  የታሪክ ፣ የባህልና የቅርስ  ሀብት ሳይተዋወቅ ተደብቆ መቆየቱን ቅር እንዳሰኛቸው ገልፀው  “ፖሎት” የተሰኘው ባለብዙ አገልግሎት የከርሰ ምድር ጎተራ የግብርና ምርቶችን  በተባይ እንዳይጠቃ ከመከላከል ባሻገር  የአርሶ አደሩን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል ።

በድንገተኛ ቃጠሎ ጊዜም አርሶ አደሩ ንብረቱ እንዳይጎዳ የሚያግዝ ባህላዊ ዘዴ መሆኑን በመግለፅ ጭምር አድናቆታቸውን ገልፀውልኛል ።

የአካባቢው ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን በጥናት በማስደገፍ በዓለም አቀፍ መድረኮች ለማስተዋወቅ  ከክልሉና ከወረዳው የመንግስት አካላት ጋር በቀጣይ አብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠውልኛል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም