ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ "በኢትዮጵያ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሉ" - በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን

99
አዲስ አበባ ሚያዚያ 28/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ "በኢትዮጵያ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሉ" የሚል እምነት እንዳላቸው በሰሜን አሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች ነዋሪ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገለጹ። ነዋሪዎቹን ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ያሳደረባቸውን ስሜት በተመለከተ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወኪል አነጋግሯቸዋል። ኢትዮጵያውያኑ በሰጡት አስተያየት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር የሚያደርጉት ንግግር ተስፋ የሚሰጥ ነው። ዶክተር አብይ ህዝቡን ለማዳመጥና አንድነትን ለማምጣት የሚያደርጉት ጥረት የሚያስደስት እንደሆነ ገልጸዋል። ይህም የአገሪቷን ለውጥ የሚያፋጥንና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን አመልክተው፤ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሊደግፏቸውና ከጎናቸው ሊቆሙ እንደሚገባም ገልጸዋል። ሲስተር ራሄል አባይ በሰጡት አስተያየት "ከንግግራቸው ውስጥ በጣም የመሰጠኝና በጣም የማደንቀው እኔም የማምንበት መደመር የሚለው ቃል ነው፣ሁላችንም አንድ ላይ ስንሆን ስንደመር ነው ውጤት የምናመጣው፤አንድንነታችንን አጠናክረን እንድንቀጥል የሚያደርጉት ጥረት በጣም ደስ የሚልና የሚበረታታ ነው፤ ሁላችንም ልናሳድገው ናልንከተለው እንዲሁም ልናግዛቸው የሚገባ ነገር ነው።"ብለዋል፡፡ አቶ ናትናኤል ረዳ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተመረጡ ጊዜ ጀምሮ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችም ይሁኑ ሌላው ሕብረተሰብ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣና ብዙ የኢትዮጵያ ሕዝብም እንደተደሰተ ገልፀው “በእርግጠኛነት እሳቸው ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው ይጠበቃሉ።" ብለዋል፡፡ አቶ አክሊል የዕብዩ እንደገለፁት “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣትነታቸው ጉልበትና ተሰሚነት አለው፤ ወጣቱ የሚኒስትሩን ኢነርጂ እያየ እሳቸውን መከተል ላይ ትኩረት ያደርጋል፣ ብዙ ጊዜ ለወጣቶች ቶሎ ብሎ የሚገባ አይነት ቃላቶችን ነው የሚጠቀሙት ያ ደግሞ ለወጣቱ ኢነርጂ ይሰጠዋል ቶሎ ተቀባይነትም ሊኖረው ይችላል ብዬ እገምታለሁ።" አቶ ቻሌ ተረፈ "ከንግግራቸው እንደተረዳሁት እሳቸው ከስልጣናቸው ይልቅ ሕዝብ የማገልገል ፍላጎታቸው ከፍተኛ የሆነ ነው ብዬ ተረድቻለሁ፤ እና ከዛም አንጻር የኢትዮጵያ ሕዝብም ከዚህ ፍላጎታቸው ተጠቃሚ ይሆናል የሚል ከፍተኛ የሆነ አመኔታ አለኝና የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህን ተረድቶ ከጎናቸው ቢሆን ቢተባበራቸው አንድ የማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ይመስለኛል።" ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ዳያስፖራው ማህበረሰብ ያደረጓቸው ንግግሮች ቀደም ሲል የሚነገሩ አሉታዊ ነገሮችን የሚያሰቀር፣ ስለ አገራቸው ያላቸውን እውነተኛ አመለካከት የሚያንጸባርቅና ተሳትፎአቸውን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል። ይህንንም በተግባር በማረጋገጥ ከአገራቸው የራቁ አንዳንድ የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት ወደ አገራቸው እንዲገቡ ያደርጋል የሚል ተሰፋ እንዳላቸውም ነው የተናገሩት። አቶ አቤል ግርማ በሰጡት አስተያየት በመላው አለም ያሉ ኢትዮጵያውያኖች ሃገር ውስጥ ካሉት ምንም ልዩነት እንደሌላቸው አድርገው በተናገሩት መደሰታቸውን ነው የገለፁት። አቶ ሳሙኤል አሰፋ "በውጭ ያሉትን መቀበላቸው ትልቅ መልዕክት ነው ሁለተኛ እንግዲህ በሚቀጥለው 6 ወር 1 አመት ምን ያህል ያንን እንደሚቀጥሉ ሰውን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ የሚያደርጉትን ማየት አለብን።" ዶክተር አብይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሰየሙ እለት ባደረጉት ንግግር ". . . ለሁላችንም የምትበቃ በዚያው ልክ ግን የሁላችንንም ተሳትፎ የምትፈልግ አገር አለችንና እውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ አገራችሁ መመለስና አገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ እጃችንን ዘርገተን እንቀበላችኋለን" ማለታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም