ኢትዮጵያና ሱዳን በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መከሩ

161
አዲስ አበባ ግንቦት 24/2010 ኢትዮጵያና ሱዳን በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች በትብብር መስራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአገሮቹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ገለጹ። ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አዲሱን የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አል_ዲልዲሪ ሞሃመድ አህመድን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። ሁለቱ ሚኒስትሮች ከውይይታቸው በኋላ በጋራ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ውይይታቸው በአባይ የውሃ አጠቃቀም፣ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ በቀጠናዊና በሁለትዮሽ በትብብር ስለሚሰሯቸው ጉዳዮች መወያየታቸውን ገልጸዋል። የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በአባይ ወንዝ፣ በቀጠናዊ፣ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲሁም በሁለትዮሽና በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም በደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ እንዲሁም የሁለቱ አገሮች መሪዎች የደረሱባቸውን ስምምነቶች ወደ ተግባር ለመቀየር በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አብራርተዋል። በኢትዮጵና ሱዳን መካከል በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ሌሎች መስኮች ያለውን የቆየ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ  መምከራቸውን ጠቁመዋል። ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ የምትከተለውን መርህ የጠበቀ አቋም አድንቀው በቀጣይም ተመሳሳይ አቋም ይዘው እንደሚሰሩ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል። የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር በሱዳን ያሉ ኢትዮጵያውያን እስረኞችን እንዲፈቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቀረበላቸውን ጥያቄ ተቀብለው መፍታታቸው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ጥንካሬ የሚያሳይ ነው በማለት ምስጋና አቅርበዋል። የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አል_ዲልዲሪ ሞሃመድ አህመድ በበኩላቸው ከዶክተር ወርቅነህ ጋር በአባይና በኢጋድ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በዚህም በቀጠናው ሰላም ለማምጣት ኢጋድና አፍሪካ ህብረት የመሳሰሉ ተቋማትን ለማጠናከርና በህዳሴው ግድብ ጉዳይም አብረው መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሱዳን ባደረጉት ጉብኝት ሁለቱ አገሮች ሁለንተናዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማመታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም