የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ክፍተቶች

335

ምናሴ ያደሳ /ኢዜአ/

የዩኒቨርስቲና ኢንዱስትሪ ትስስር የአሰራር መመርያ ተዘጋጅቶለት ወደ ስራ ከተገባ አመታት ተቆጥረዋል፡፡

አሰራሩ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ አዳዲስ እውቀቶችንና የምርምር ውጤቶችን  በማምረቻና አገልግሎት መስጫ ተቋማት በቅንጅት ጥቅም ላይ ለማዋልና የተማሪዎችን የተግባር እወቀት ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ታምኖበታል ። ወጪን በመቆጠብ ሀብትን በጋራ በጋራ ለመጠቀም ጭምር ይረዳል ። 

ትስስሩን ለማጠናከርም መንግስት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ፖሊሲ ቀርጾ እየተገበረ ይገኛል፡፡ በኢኖቬሽን ፖሊሲው ከተለዩ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የዩኒቨርስቲ ፣የቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ተቋማት፣ የምርምር ማእከላትና ኢንዱስትሪ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡

የተቋማቱ ትስስር እያስገኘ ያለው ውጤቶችንና ችግሮቻቸውን ለመለየትና የመፍትሄ  ሀሳብ ለማፍለቅ ያለመ የምክክር መድረክ ሰሞኑን በመቱ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ ከሀገሪቱ ተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ የኢንዱስትሪ፣ የማምረቻና አገልግሎት መስጫ ተቋማት የተሳተፉ ሲሆን በአብዛኛው በትስስሩ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማንሳት ተወያይተዋል፡፡ የመፍትሄ ሀሳብ ነው ያሉትንም አስቀምጠዋል፡፡

የትስስር መመሪያው  በዩኒቨርስቲና በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ማዕከላት የሚሰጡ ትምህርትና ስልጠናዎች ከኢንደስትሪ ፍላጎት ጋር ተጣጥመው እንዲሰጡ  ማድረግ አንዱ አላማው ነው፡፡

የልማት ፕሮግራሞችና የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ከማረጋገጥ አኳያ ያደጉ ሀገራትን ቴክኖሎጂ በማስገባትና በማላመድ ዩኒቨርስቲዎችና የምርምር ተቋማት ለኢንዱስትሪዎች የማማከር ድጋፍ እንዲሰጡ ማድረግም ሌላው ነው፡፡

የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም በኢንዱስትሪ ተቋማት የተግባር ስልጠና እንዲወስዱ ማድረግ ሌላኛው ነው፡፡

በመድረኩ ከተነሱት ችግሮች መካከል በዩኒቨርስቲና ተቋማቱ መካከል ያለው አሰራር ያልተቀናጀ መሆን፣ ለተግባር ልምምድ  የሚላኩ ተማሪዎች ከክትትልና ድጋፍ ማነስ የተነሳ በሚፈለገው ደረጃ የተግባር እውቀት ቀስመው ያለመውጣት ይጠቀሳሉ፡፡

ለዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስሩ ውጤታማነት ሁሉም አካላት በእኩል ደረጃ ሀላፊነታቸውን ያለመወጣትና የአሰራር መመሪያው ክፍተትም አንዱ ተግዳሮት ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች በተቋማት አካባቢ የሚገኙ ንድፈ ሀሳብና ተግባሩን በአግባቡ የሚገኙ ባለሙያዎችን በመጋበዝ የመጠቀም ችግር እንዳለም ተነስቷል፡፡

የዩኒቨርስቲ መምህራንም  በኢንተርንሺፕ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በመደበኛነት በተቋማት በመገኘት ክህሎታቸውን የማሳደግ ስራም ሊሰራ እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

 የትስስር መመሪያው ተግባራዊነት በኢንዱስትሪው ላይ ብቻ ማተኮሩና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከኢንደስትሪው እኩል ኃላፊነታቸውን ያለመረዳት እና ያለመወጣት ተነስተዋል ።

 ዩኒቨርሲቲዎች ለጋራ ምርምር በጀት መድቦ ለመስራት ያላቸው ተነሳሽነት ውስን መሆን፤ አብዛኛው ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮግራሙን የሚመራ ቋሚ አካል (focal person) ያለመመደብና የተመደበውም አካል በትምህርትና በዝውውር ወይም በሌላ ምክንያት ዩኒቨርሲቲውን ሲለቁ ተግባሩ ባለቤት አልባ መሆኑ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የአምቦ ማዕድን ውሀ ፋብሪካ ተወካይ አቶ ደሳለኝ መኮንን እንዳሉት በመስኩ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎቻቸውን ለተግባር ልምምድ ወደ ተቋማት ሲልኩ መርሀ ግብሩን ለማሟላት እንጂ ተማሪዎቹ መቅሰም ስላለባቸው ዕውቀትና ክህሎት በቂ ጥናትና ዝግጅት አያደርጉም፡፡

በዩኒቨርስቲና በኢንዱስትሪዎች መካከል ያለው ትስስር ከትብብር ባለፈ አስገዳጅ መመሪያ ተዘጋጅቶለት ባለመሰራቱ የትኩረት ማነስ በሁለቱም ወገን ይታያል ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተማሪዎች ቸልተኛ እንዲሆኑና ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ እያደረገ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

እንደ አምቦ ማዕድን ውሀ ፋብሪካ በየጊዜው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን መቀበል በተግባር የተደገፈ ስልጠና ቢሰጥም ቀስመው የሚወጡት እውቀትና ክህሎት በሚፈለገው ደረጃ አይደለም ያሉት አቶ ደሳለኝ ለዚህም ምክንያቱ ዩኒቨርስቲዎች የተማሪዎቻቸውን ክፍተት በመለየት ተማሪዎችን በአግባቡ ያለመላካቸው ነው ይላሉ፡፡

ከኢንዱስትሪ ተቋሙ አቅም ማነስ እና የክትትል ማነስ የተነሳ ተማሪዎቹን በአግባቡ የመደገፍ ክፍተቶች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡

የአገልግሎት ሰጪና ማምረቻ ተቋማት  ለተማሪዎቹ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ  ለመርሀ ግብሩ የሚያወጡትን ወጪ የሚያካክሱበትን ድጋፎች ከመንግስት ሊያገኙ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ለምሳሌ በታክስ ህጉ በ corporate social responsibility  የሚወጡ ወጪዎች በተወሰነ መልኩ ከገቢ ግብር ተቀናሽ ሆነው በወጪ የሚያዙበት አሰራር አለ ያሉት አቶ ደሳለኝ ፣  በፕሮግራሙ የሚወጡ ወጪዎችን ከገቢ ግብር ታክስ ተቀናሽ ሆነው በወጪነት እንዲያዙ መንግስት በመመሪያ ሊያካትተው እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የሀብት ብክነት እንዳይፈጠርና  የዩኒቨርስቲ የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ  የቴክኒክና ሙያ፣ጤና እና ምርምር ተቋማት በስፋት ማካተት እንዳለበት አንስተዋል፡፡ በኢንዱስትሪዎች የምርምር ማዕከላት በብዛት ያለመገኘትም አንዱ ተግዳሮት ነው፡፡ 

ትስስሩ ውጤታማ እንዲሆን በኢንዱስትሪዎች የምርምር ማዕከላት በማጠናከር በዘርፉ በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከርና የጋራ ተጠቃሚነት ስሜት እንዲዳብር  ዩኒቨርስቲዎች በተቋማት ውስጥ ለሚገኙ ባለሙያዎች የትምህርት እድል ማመቻቸት  እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች  አካባቢ የሳምንት መጨረሻ ትምህርት መስጫ ማዕከላትን ቢገነቡ ተማሪዎች በአቅራብያቸው በተግባር የተደገፈ ስልጠና በመውሰድ ውጤታማ ከመሆናቸውም ባለፈ በዩኒቨርስቲና ኢንዱስትሪ መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ፡፡

የመቱ ዩኒቨርስቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ጥናትና ምርምር ትስስር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጸጋዬ በርኬሳ እንዳሉት ለዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስሩ በሚፈለገው መጠን ውጤታማ ያለመሆን ከምክክር መድረኩ ሰፊ ግንዛቤ ተገኝቷል ይላሉ ፡፡

በዩኒቨርስቲው በኩል ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት እና በኢንዱስትሪ ተቋማት አካባቢ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ  በጋራ መግባቢያ ሰነድ  ትስስሩን ለማጠናከር ዩኒቨርስቲው በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ እንደ ችግር ከተነሱት መካከል ወደ ኢንዱስትሪዎች ለተግባር የሚላኩ ተማሪዎችን የመከታተልና በአግባቡ የማሰራት ችግር መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርስቲው ይሄንን ችግር ለመቅረፍ የተጠናከረ የክትትልና ድጋፍ አሰራር በመዘርጋት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርስቲው ምሁራንም በእንደስትሪዎች የሙያ እገዛና ድጋፍ እና የምክር አገልግሎት  እንዲሰጡና  በእንደስትሪዎች አካባቢ በሚታዩ ችግሮች ዙሪያ ችግር ፈቺ የምርምር ስራ በጋራ ለመስራት ዩኒቨርስቲው መዘጋጀቱን ነው የተናገሩት፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር  አቶ እንግዳዬ መርሻ እንዳሉት የኢንዱስትሪ ዩኒቨርስቲ ትስስር አላማ ሀብትን በጋራ የማቀድና የኢንዱስትሪውን የተወዳዳሪነት አቅም ለማሳደግ ነው፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የብሄራዊ የሳይንስና ኢኖቬሽን ፎረም  ተቋቁሞ  በዩኒቨርስቲና ተቋማት መካከል የመደጋገፍ ፣የጋራ መግባባትና ተጠቃሚነት እንዲኖር እየሰራ ይገኛል፡፡

ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ ያለው የዩኒቨርስቲ እና እንደስትሪ ትስስር  መመርያ ያሉበትን ክፍተቶች ለመሙላት የምክክር መድረኩ ትልቅ ግብአት መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ዩኒቨርስቲ ትስስር ሲባል በአብዛኛው በዩኒቨርስቲዎች ላይ ብቻ የማተኮር ችግር ይታያል ያሉት አቶ እንግዳዬ  ትስስሩ ከዚህ ባለፈ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት እና የምርምር ተቋማትን የማስተሳሰር ስራ  ተጠናክሮ እንዲቀጥል ስራዎች ይሰራሉ፡፡

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍና በአሰራር መመርያው ላይ  የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላትና የተለያዩ ሀሳቦችን ለማካተት በቅርቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ  ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር ፎረም እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ የሚካሄደው የጋራ ፎረም ሁሉንም የሚመለከታቸው አካላትን ስለሚያሳትፍ ችግሮችን በመለየትና በትስስሩ የሁሉም አካላትን የባለቤትነት ተሳትፎ  በማጠናከር ውጤታማ ስራ ለመስራት መታቀዱን አብራርተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ዩኒቨርስቲዎችን፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትንና የምርምር ተቋማትን እንዲሁም እንደስትሪዎችን ያካተቱ 24 የትስስር ፎረሞች የተቋቋሙ ሲሆን በስራቸውም የልማት ኮሪደሮችን መሰረት ያደረጉ 17 የቀጠና ፎረሞች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡