ኢጋድ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ቡድኖችን ፊት ለፊት ሊያገናኝ ነው

84
አዲስ አበባ ግንቦት 24/2010 ኢጋድ የደቡብ ሱዳን ተቃራኒ ሃይሎችን ፊት ለፊት ለማገናኘት ወሰነ። የሰላም ሂደቱን የሚያደናቅፉና የተደረሱትን ስምምነቶች የሚጥሱ ግለሰቦች ላይ ደግሞ እርምጃ እወስዳለው ብሏል ኢጋድ። የምስራቅ አፈሪካ አገራት የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭትን በተመለከተ ትናንት በአዲስ አበባ በዝግ ሲመክር ውሏል። ውይይቱን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት ኢጋድ በትናንትና  ስበሰባው የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪርና የቀድሞ ምክትላቸው ዶክተር ሪክ ማቻርን ፊት ለፊት አገናኝተው ችግሮቻቸው ላይ እንዲወያዩ ለማድረግ ወስኗል። ይህ እንዲሆን ኢጋድ የመሪነት ሚና ይወጣል ብለዋል ዶክተር ወርቅነህ ። ከዚህም በተጨማሪ ኢጋድ በትናንት ስብሰባው በደቡብ ሱዳን የሚደረገውን የሳላም ሂደትና ምክክሮች የሚያደናቅፉ ሃይሎች ላይ ማዕቀብ ለመጣል መዘጋጀቱን ነው የገለጹት። "ወንድምና እህት ደቡብ ሱዳናዊያን ከጎሮበቶቻቸው ሰላም እንዲወርድላቸው እየተጠባበቁ ነው" ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፤ ሰላም ለማምጣት የሚደረገው ሂደት ውስጥም ይህ ሌላ ምዕራፍ የሚከፍት እና በቅርቡ እንደሚተገበርም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ኢጋድ ባሳልፍነው ሳምንት ለደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማውረድ የሚረዳ  አዲስ የሳላም ድርድር ምክረ ሃሳብ አዘጋጅቻለው ማለቱ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም