በደቡብ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ ዘመናዊ ሥርዓት ለመዘርጋት ዝግጅቱ ተጠናቋል

96

ሐዋሳ መጋቢት 17/2011 በክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ ዘመናዊ ሥርዓት ለመዘርጋት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  አገልግሎት  ቢሮ ገለጸ፡፡

ቢሮው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው የክልሉ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳባቸውን በዘመናዊ መንገድ የሚፈጽሙበት አሰራር በቅርቡ ይተገበራል።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ሥራ ላይ በሚውለው አሰራር ከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች ሲሆኑ፣ይህም የኢንዱስትሪ ደንበኞች፣የግል ድርጅቶችና መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ያካትታል፡፡

በተጨማሪም ፈቃደኛ የሆኑ ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች ሊሆኑበት ይችላሉ ብሏል፡፡

አሰራሩ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ክፍያ ለመፈጸም የሚያጠፉትን ጊዜ እንደሚያሳጥር አስታውቋል፡፡

አሰራሩ ግልጽና በደረሰኝ ስለሚከናወን ለክትትልና ቁጥጥር እንደሚያመችም ገልጿል፡፡

የደንበኞች መረጃ በባንኩና በተቋሙ በጥንቃቄ እንደሚያዝ ከመያዙም በላይ በኢሜልና በአጭር የጽሁፍ መልዕክት እንዲደርሳቸው ይደረጋል ብሏል፡፡

የደንበኞች መሠረታዊ መረጃ የማሰባሰብ እየተሰባሰበ ነው ያለው ተቋሙ፣ አሰራሩ የሚተገበረው ደንበኞች የሚጠበቅባቸውን መረጃ ከሰጡና ከተቋሙ ጋር ውል ከፈጸሙ በኋላ መሆኑን አስረድቷል፡፡

በመሆኑም ከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚ ደንበኞችና ፈቃደኛ የሆኑ ዝቅተኛ ኃይል ተጠቃሚዎች በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ አገልግሎት መስጫ ማዕከል በመሄድ ለስምምነት የተዘጋጀውን ቅፅ እንዲሞሉ ጠይቋል፡፡

በደቡብ ክልል የኤሌከትሪክ አገልግሎት የሚሰጡ በሐዋሳ፣በወላይታ፣በሆሳዕና፣በአርባምንጭና በቦንጋ በሚገኙ ዲስትሪክቶች አሰራሩ ይተገበራል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳባቸውን በባንክ የሚፈጽሙበትን የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የተፈራረመው ጥር 13/2011 ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም