የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ለጓደኛው ሲፈተን ተገኝቷል የተባለ የዩኒሸርስቲ ተማሪ ተያዘ

1426

አርባምንጭ ግንቦት 24/2010 በጋሞ ጎፋ ዞን ጨንቻ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የአስረኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለጓደኛው ሲፈተን ተገኝቷል የተባለ የዩኒቨርሲት ተማሪ መያዙን የዞኑ የብሔራዊ ፈተናዎች ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።

የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ አቶ ማሄ ቦዳ ለኢዜአ እንደተናገሩት ተማሪው ሊያዝ የቻለው በትምህርት ቤቱ ትናንት የተሰጠውን የጠዋት የሂሳብ ፈተናን ለጓደኛው ሊፈተን እጅ ከፍንጅ በመያዙ ነው።

ሀሰተኛ የመፈተኛ መታወቂያ ይዞ ከገባ በኋላ በጥርጣሬ እንደተደረሰበትም አመልክተዋል፡፡

ግለሰቡ  በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ ዓመት የሲቪል ምህንድስና ተማሪ እንደሆነ በተደረገው ማጣራት መረጋገጡንም አስታውቀዋል።

የራሱን ፈተና ለሌላ ሰው አሳልፎ በመስጠት የተጠረጠረው የትምህርት ቤቱ ተማሪም አብሮ ተይዟል።

ሁለቱም ተማሪዎች በጨንቻ ወረዳ አቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባቸው  ዛሬ ጠዋት ለፍርድ መቅረባቸውንና ውሳኔያቸውንም እየተጠባበቁ እንደሚገኙ  አቶ ማሄ ጠቅሰዋል።

ከዚህ ውጭ በዞኑ እየተሰጠ ያለው የአስረኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በመልካም ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።