የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ የምክክር መድረክ በናይሮቢ ይካሄዳል

79

ናይሮቢ መጋቢት 16/2011 የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ የምክክር መድረክ በመጪው ሚያዚያ ወር በናይሮቢ የሚካሄድ መሆኑን የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

በኬንያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ የናይሮቢ የአስተባባሪ ኮሚቴ የምክክር መድረክ  ሚያዚያ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በኬንያ መዲና ናይሮቢ ይካሄዳል።

በዚህ ጉዳይ የኮሚቴው አባላት ከኢፌዲሪ አምባሳደር መለስ ዓለም ጋር በስፋት መክረዋል።

የምክክር መድረኩ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የበለጠ መቀራረብና ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህል እንዲለጎብት ማድረግን ዓላማ ያደረገ መሆኑንም በዚሁ ጊዜ ጠቅሰዋል።

በዲያስፖራው ጠንሳሽነትና አስተባባሪነት የሚካሄደው የምክክር መድረክ ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን በተግባር የሚያረጋግጥ አጋጣሚ መሆኑንም እንዲሁ።

አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው የኢትዮጵያ ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ በመሆኑ ለመድረኩ መሳካት በናይሮቢ የሚገኘው ኤምባሲ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ለኮሚቴው አባላት ገልፀውላቸዋል።

የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ በሚገኝ መዋጮ  በኢትዮጵያ የሚታዩ ማህብረሰባዊ የልማት ክፍትቶችን ለመሙላት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ ጠንሳሽነት መቋቋሙ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም