ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጀ

81

አዳማ መጋቢት 16/2011 ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ረቂቅ ፖሊሲ ማዘጋጀቱን የሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ።

ስለረቂቅ ፖሊሲው ግንዛቤ ለማስጨበጥና የማዳበሪያ ሀሳብ ለማሰባሰብ ሚኒስቴሩ ለባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል።

በሚኒስቴሩ የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ማቲያስ አሰፋ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በተለያዩ አካላት የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን በማቀናጀት ውጤታማና ዘላቂ  አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል ፖሊሲ ማዘጋጀት አስፈልጓል።

ፖሊሲው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚመራበትን የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋትና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች ዕውቅና ለመስጠት የሚያስችል ነው።

ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ፖሊሲው ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

የፖሊሲው መውጣት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በሃገሪቱ የልማት እቅዶችና መርሃ ግብሮች  ውስጥ ለማካተት እንደሚያስችል  ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በመንግሥትና በማህበረሰቡ ያልተሸፈኑ የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት ፖሊሲው የሚያበረክተረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነም አመልክተዋል።

ፖሊሲው  በሀገር ውስጥና ውጭ የሚኖሩ  ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 35 ድረስ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

በፖሊሲ ዝግጅቱ ወቅት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ታይላንድ፣ኬንያና ሩዋንዳ ልምዶችን እንደ መነሻ ተወስደዋል፡፡

ረቂቅ ፖሊሲው በተያዘው በጀት ዓመት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

የፖሊሲውን መጽደቅ ተከትሎም ተጠሪነቱ ለሴቶች፣ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒሰቴር የሆነ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተዳደር ኤጀንሲ እንደሚቋቋም ተመልክቷል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮዽያ ወጣቶች ፌዴሬሽን የበጎ ፈቃድ ዘርፍ ዋና አስተባባሪ ወጣት  በአምላክህ ታደሰ  የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባለቤት አልባ በመሆኑ የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ ማድረጉን ተናግሯል።

ወጣቱ እንዳለው የፖሊሲው መውጣት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ አደረጃጀት እንዲኖረውና ውጤታማ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

በአማራ ክልል ሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የወጣቶች ማካተት ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አወቀ መንግሥቴ በበኩላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውጤታማ እንዲሆን የሚያፈልገውን ጠቁመዋል፡፡

ይህም ከሚኒስቴሩ ባለፈ ሁሉም የመንግስት ተቋማት ኃላፊነታቸውን በለየ መልኩ መመሪያ ተዘጋጅቶ ስራ ላይ እንዲውል በፖሊሲው በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት ነው።

የውይይት መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም