በአዲስ አበባ ህዳሴ ግድብ 8ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ አውደ ርዕይ ተከፈተ

138

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2011 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን ስምንተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የፎቶ፣ ቅርጻ ቅርጽና የስዕል አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሚኒሊክ አደባባይ ተከፈተ። 

አውደ ርዕዩ ዛሬን ጨምሮ እስከ መጋቢት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ለጎብኝዎች ክፍት መደረጉም ታውቋል።  

በመርሃ ግብሩ ላይ የግድቡ ግንባታ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ እንዲሁም በተማሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች እና ሌሎችም አካላት መጎበኘቱን የሚያሳዩ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

በግድቡ ላይ የተቀዛቀዘውን የሕዝብ ድጋፍ እንዲያንሰራራ በማድረግ በኩል መሰል መርሀ ግብሮች የላቀ ሚና ይኖራቸዋልም ነው የተባለው።

በአዲስ አበባ ከተማ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዘውዱ ገብረኪዳን እንደተናገሩት፤ የግድቡ ግንባታ ከተበሰረ ዕለት አንስቶ የከተማዋን ነዋሪዎች በማስተባበር 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚገመት ኃብት ማሰባሰብ ተችሏል።

''የሕዝቡ ተሳትፎ በፊት የነበረውና የአሁኑ ሲነጻጸር እኩል አይደሉም ''ያሉት ኃላፊዋ በቀጣይ ግድቡ ተጠናቆ ሕዝቡ ተፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኝ ድጋፉን እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል።   

የግድቡ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ነዋሪው በእድሜ፣በኃይማኖትና በኑሮ ደረጃ ሳይገደብ ድጋፍ ሲያደረግ እንደነበር አስታውሰው አሁንም ድጋፉ እንዲቀጥል ሕዝቡን የሚያንቃቁ ሥራዎች በስፋት ሊከናወኑ ይገባል ብለዋል። 

የአውደ ርዕዩ ተሳታፊ አቶ ሱልጣን ጋሩምሳ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት የግድቡ ግንባታ ተጓትቷል መባሉን ተክትሎ የተወሰነ መቀዛቀዝ እንደነበር አስታው አሁን ግን ሁሉም መረባረብ አለበት ብለዋል።    

ግድቡን በሚመለከት ትክክለኛና ወቅታዊ  መረጃ ለሕዝቡ ተደራሽ በማድረግ የሕዝቡን ተሳትፎ ማጎልበት እንደሚገባም አሳስበዋል። 

የመንግሥት ደሞዝተኛ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ሱልጣን ''ከልጆቼ ጉሮሮ ላይ ቀንሼ እስካሁን 8 ሺህ ብር ለግድቡ ድጋፍ አድርጊያለሁ፤ ችግሮች ቢያጋጥሙም ለቀጣዩ ትውልድ ታሪክ ሰርተን እንለፍ'' ብለዋል።   

ሌላው የአውደ ርዕዩ ተሳታፊው ወጣት ሙሉጌታ ላቃቸው በበኩሉ "ምንም እንኳን ግድቡ በተባለው ግዜ ኃይል ባያመነጭም ፤ችግር ቢገጥመውም የአገር ኃብት ነውና መጠናቀቅ ይኖርበታል" የሚል ሀሳብ አካፍሎናል።   

ሕዝቡ በይበልጥ እንዲነቃቃና ለግድቡ የሚሰጠውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ለማድረግ በመገናኛ ብዙሃን የሚያንቃቁ ስራዎች መከናወን ላይ ትኩረት ቢደረግ በማለትም አስተያየን ሰጥቷል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም