ዐቃቤ ህግ አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግ ጠየቀ

97

አዲስ አበባ  መጋቢት 16/2011 የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግለት ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ጠየቀ።

በእነ አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ የክስ መዝገብ 1ኛ. አቶ አብዲ ዩሱፍ መሐመዶ (ያልተያዙ)፣ 2ኛ. አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ፣ 3ኛ አቶ መሐመድ አህመድ (ያልተያዙ) እና 4ኛ. አቶ አብዱላሂ ሁሴን (ያልተያዙ) ሰዎች ከ15 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወቃል።

2ኛ ተከሳሽ አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ''የተከሰስኩት በሱማሌ የትምህርት ቢሮ የመጽሕፍት ህትመትን በተመለከተ በመሆኑ ክሱ በክልሉ እንዲታይልኝ'' ሲሉ ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የተከሳሹ ጉዳይ በፌዴራል መንግስት የተመዘገበ እና ከአንድ ክልል በላይ የሚንቀሳቀስ ሕዝባዊ ድርጅት ከሆነው ኒያላ ኢንሹራንስ የስራ ኃላፊ ጋር በመመሳጠር የተፈጸመ ወንጀል እንደሆነ አስረድቷል።

በአዋጅ ቁጥር 883/2007 አንቀጽ 6 መሠረት ከአንድ በላይ በሆኑ ክልሎች በሚንቀሳቀሱ ሕዝባዊ ድርጅቶችና ሰራተኞ የሚፈጸም የሙስና ወንጀል በፌዴራል መንግስት ስር የሚወድቅ መሆኑን አመልክቷል።

አቶ ቴዎድሮስ የተከሰሱበት የክልሉ የመጽሐፍት ህትመት በጀት ከፌዴራል መንግስት ድጐማ ጋር የተያያዘ መሆኑን በክልሉ መረጋገጡን አመልክቶ ጉዳዩ በሂደት በመደበኛ ክርክር በማስረጃ የሚረጋገጥ እንደሆነ ዐቃቤ ህግ ባቀረበው መቃወሚያ ላይ ተብራርቷል።   

በቀረበው ክስ ላይ የተፈጸመው የሙስና ወንጀል ከባድ ዓላማ በዝርዝርና በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን የዳኝነት ስልጣን ያለው ክሱ የቀረበለት ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሆኑ ተከሳሽ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግለት ዐቃቤ ህግ ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ የአቶ ቴዎድሮስን የክስ መቃወሚያና የዐቃቤ ህግን ጥያቄ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም