ለፓርኩ ግንባታ ከይዞታቸው የተነሱ አርሶ አደሮች ቃል የተገባላቸው ልማት እንዲፈጸም ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

62

አዳማ  መጋቢት 16/2011 ለአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ከይዞታቸው የተነሱ  አርሶ አደሮች ቃል የተገባላቸው የመሰረተ ልማት አቅርቦት ተፈጻሚ እንዲሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በቅርቡ ተመርቆ ወደ ሥራ የገባውን የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

የአባላቱ ቡድን መሪ አቶ ጌታቸው ለማ  እንደገለጹት የፓርኩን ልማነትና በተጓዳኝም የአካባቢውን  ለልማት  ተነሽ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ያለውን እንቅስቃሴ በመስክ አይተዋል።

የክልሉ መንግስት ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው ምትክ ቦታ መስጠቱን አድንቀው ሆኖም  ሴቶችና ወጣቶች እስካሁን የንግድና መስሪያ  ቦታ ባለማግኘታቸው ቅሬታ እንዳላቸው ተመልክተዋል፡፡

በተለይም ከእርሻ መሬታቸው የተነሱ አርሶ አደሮች ተገቢውን የመሰረተ ልማት ለማቅረብ  ቃል የተገባላቸው የመብራት፣ውሃና የመንገድ መሰረተ ልማት አቅርቦት እንዳልተፈጸመ በመስክ ምልከታው ወቅት መገምገማቸውን ቡድን መሪው ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣የክልሉ መንግስትና የከተማዋ አስተዳደር የልማት ተነሺ  አርሶ አደሮች ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በትብብር መስራት እንዳለባቸው  አሳስበዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በፓርኩ  የተገነቡ 19 የማምረቻ ማዕከላት በባለሃብቶች መያዛቸው  በጥንካሬ የተመለከተ ሲሆን አንድ የቻይና ኩባንያ ብቻ ወደ ምርት መግባቱ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ፈጥነው ወደ ማምረት እንዲገቡ አመላክተዋል።

በግንባታ ላይ የሚገኘው የቻይና ሳንሻይን ኩባንያ የብረታ ብረትና ማሽነሪዎች ማምረቻ  በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዳማ ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብደላ ገሞ በበኩላቸው የእርሻ መሬታቸውን የለቀቁ አርሶ አደሮች በወቅቱ የኢንዱስትሪ ፓርኩን  ሲጠየቁ  መንገድ፣ውሃና መብረት እንደሚገባላቸው በመንግስት ቃል ተገብቶላቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ቀጥታ ወደ ግንባታ በመገባቱ አሁን አርሶ አደሮቹ የመውጫና መግቢያ መንገድ እንዲሁም የመጠጥ ውሃ ችግር እንዳጋጠማቸው ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል፡፡

የመኖሪያ ቤት ምትክ ቦታ 2ሺህ ለሚጠጉ አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው መሰጠቱን ገልጸው  የማምረቻና መስሪያ ቦታ ላልተሰጣቸው እንዲያገኙ  የከተማዋ አስተዳደር  አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

"ከአስተዳደሩ አቅም በላይ የሆኑት በተለይም በክልልና በፌዴራል መንግስት ደረጃ ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ቃል የተገባው የመሰረተ ልማት አቅርቦት እስካሁን  አልተፈፀመም "ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ለአርሶ አደሮቹ ቃል የተገባው የመሰረተ ልማት አቅርቦት ጉዳይ በክልልና በፌዴራል ደረጃ የሚመለከታቸው አካላት ተፈጸሚ እንዲያደርጉ ለመከታተል አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም