ቀጣዩ ምርጫ ነጻ፣ ገለልተኛና ፍትሃዊ እንዲሆን የምርጫ አሰፈጻሚ አካላት ስነ-ምግባር ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል-አስተያየት ሰጪዎች

151

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2011 ቀጣዩ ምርጫ ነጻ፣ገለልተኛና ፍትሃዊ እንዲሆን የምርጫ አሰፈጻሚ አካላት ስነ-ምግባር ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ጠየቁ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባዘጋጀው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ዶክተር ጌዴኦን ጢሞቲዮስ የረቂቅ አዋጁን ይዘት ለውይይት አቅርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ቀጣዩ ምርጫ ነጻ፣ ገለልተኛና ፍትሃዊ እንዲሆን የምርጫ አሰፈጻሚ አካላት ስነ-ምግባርን በሚመለከት በረቂቅ አዋጁ ላይ በትኩረት እንዲካተት ጠይቀዋል።

የምርጫ አስፈጻሚ አካላት ሙሉ ለሙሉ ገለልተኛ መሆን ምርጫው ከመልካም አስተዳደር ችግር መጻዳት ያስችለዋል ብለዋል።

የህዝብና ቤት  ቆጠራ ሳይካሄድ የሚኖር ምርጫ የተጭበረበረና ኢፍትሃዊ ይሆናል የሚል ስጋት እንዳላቸውም አንሰተዋል ተሳታፊዎቹ።

የምርጫ አስፈጻሚ አካላት የየትኛውም ፓርቲ አባል መሆን እንደሌለባቸው ግልጽ አቅጣጫ የተቀመጠ ቢሆንም ላለፉት ግዜያት ሲካሄድ በነበረው ምርጫ ተሳትፏቸው ወደ አንድ አካል ያዘነበለ እንደነበርና በዚህም ምክንያት ፍትሃዊ ምርጫ ሳይካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አሁንም አስፈጻሚ አካላቱ ከየትኛውም ፓርቲ አመለካከት የጸዱና በስነ  ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ አዋጁ በዝርዝር አቅጣጫ ማስቀመጥ እንዳለበትና በዚህም ተግባራዊነቱን መከታተል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም የስራ አመራር ቦርድ አባላት ቁጥር አሁን ካለው የፓርቲ ብዛት ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ ዝቅተኛ በመሆኑ ይህም ከፍ እንዲልና ተደራሽነታቸው እንዲሰፋ ለማድረግ አዋጁ በድጋሜ ሊታይ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የምርጫ አስፈጻሚ አካላት ምልመላ፣ የምርጫ ጣቢያ ልየታ፣ ዘመናዊ የኮሮጆ አጠቃቀም፣ ለምርጫ ቅስቀሳው የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምና ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከትም እንዲሁ በአዋጁ በዝርዝር ሊዳሰስ እንደሚገባ አክለዋል።

ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ዶክተር ጌዴኦን ጢሞቲዮስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ከኢትዮጵያ ሳይንሰ አካዳሚ፣ ከኢትዮጵያ ሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ንግድና ማህበራት ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ከሲቪል ማህበራትና ከአገር ሽማግሌዎች የተወጣጡ የስራ አመራር ቦርድ አባላትን የሚመለምል ገለልተኛ ኮሚቴ ያቋቁማል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ኮሚቴውም ከህዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከሲቪል ማህበራት የስራ አመራር ቦርድ አባል ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን ጥቆማ የሚቀበልበት አንቀጽ በአዋጁ ማካተቱን ገልጸው፤ የተመረጡትን እጩዎች ለህዝቡና ለጠቅላይ ሚኒስስትሩ ይፋ የማድረግ ተግባር ያከናውናል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከእጩዎቹ፣ ከስራ አመራር ቦርድ አባላትና ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር በመሆን ምክክር የሚያደርጉ ይሆናልም ብለዋል።

በቀጣይም ከምክክሩ የተገኙ ግብዓቶችና ማሻሻያዎችን በማከል የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢን፣ ምክትል ሰብሳቢንና አባላትን ለህዝብ ለሹመት ያቀርባሉ ያሉት ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፤ ምክር ቤቱም በአባላቱ ሙሉ እምነት ካለው ሹመቱን ያጸድቃል ብለዋል።

ይህ አሰራር ከገለልተኝነትና ከስነ-ምግባር መጓደል ጋር ተያይዞ ለሚነሳው ቅሬታም ምላሽ ለመስጠት የሚያግዝ ነው።  

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ቋሚ ኮሚቴው ከአስፈጻሚ አካላት ምልመላና ሌሎች በዝርዝር የሚታዩ ጉዳዮችን በድጋሚ እንዲታይና ማሻሻያ እንዲደረግበት ውይይቱ ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል።

የቦርዱ ስልጣንና ኃላፊነት፣ የስራ ዘመንና በአባላት የሚነሱ ቅሬታዎች አፈታት ተፈጻሚነትና ሌሎች ሃሳቦችንም እንዲሁ በዝርዝር እንዲታዩና አዋጁ ውስጥ መካተት ያለባቸው ሃሳቦችን በማካተት ረገድ በድጋሜ ታይቶ እንዲጸድቅ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም