ባገኘነው ብድር ተጠቅመን ውጤታማ ስራ በማከናወን ላይ ነን – በወላይታ ዞን በማህበር የተደራጁ ወጣቶች

842

ሶዶ ግንቦት 24/2010 ባገኙት ተዘዋዋሪ ብድር በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ ስራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን በወላይታ ዞን  በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ገለጹ፡፡

ካለፈው ዓመት ሃምሌ ወር ጀምሮ በማህበር ለተደራጁ ከ800 በላይ ኢንተርፕራይዞች 90 ሚሊዮን ብር በብድር ማሰራጨቱን የዞኑ ከተማ ልማትና ቤቶች መምሪያ ገልጿል፡፡

በዞኑ በአረካ ከተማ 03 ቀበሌ የቤትና የቢሮ ዕቃ ማምረቻና መሸጫ ማህበር አባል ወጣት ፍቃዱ ሶርሳ እንዳለው አምስት ሆነው በመደራጀት ባገኙት 200 ሺህ ብር ብድር  ወደ ስራ ገብተዋል፡፡

በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ጠንክረው በመስራት በአሁኑ ወቅት ከሚያገኙት ገቢ ላይ ብድራቸውን ከፍለው 150 ሺህ ብር መቆጠብ መቻላቸውን ገልጿል፡፡

በቀጣይ የበለጠ ለመስራት በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ገልፆ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ጠይቋል፡፡

በከተማዋ 02 ቀበሌ እንስራ የባልትና ውጤቶች ማህበር አባል ወጣት ሰማያት ነጋ በበኩሉ በተያዘው ዓመት መስከረም ወር ላይ በብድር ባገኙት 63 ሺህ ብር የተለያዩ የባልትና ውጤቶችን አዘጋጅቶ በማቅረብ ስራ መሰማራታቸውን ተናግሯል ፡፡

ብድር በመፍራት በፍጥነት ወደ ስራ አለመግባታቸው እንደጸጸታቸውና በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ እዳቸውን በመክፈል በአይነት ያለው ሳይጨምር 58 ሺህ ብር ትርፍ ማግኘታቸውን ጠቁሟል፡፡

በወላይታ ሶዶ ከተማ በመስታወት ስራ አምስት ሆነው በመደራጀት ከተዘዋዋሪ ፈንድ ባገኙት የ200 ሺህ ብር ብድር ወደ ስራ በመግባት ውጤታማ መሆናቸውን የተናገረው ደግሞ የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ምትኩ ማርቆስ ነው፡፡

”ተደራጅተን ወደ ስራ በመግባታችን ከእያንዳንዳችን ያለውን የተለያየ ዕውቀትና ልምድ በማደራጀት በአጭር ጊዜ ተወዳዳሪ ለመሆን በቅተናል” ያለው ወጣት ምትኩ በአሁኑ ሰዓት ከ300 ሺህ ብር በላይ ሀብት ማፍራታቸውን ገልጿል፡፡

የዞኑ ከተማ ልማትና ቤቶች መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጎአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በ892 ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ 5 ሺህ ወጣቶች 90 ሚሊዮን ብር በብድር ተሰራጭቷል፡፡

ለመስሪያና ለመሸጫ ከ20 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የ339 ሼዶች ግንባታ መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡

የገበያ ትስስር በተገቢውና ወጥ በሆነ መልኩ ያለመፈጠሩ፣ የብድር አቅርቦት አሰራር ቀልጣፋ ያለመሆኑ፣ የብድር አመላለስ ደካማ መሆኑና ስራ ሊፈጠርላቸው ከሚገባው ወጣት ቁጥር አንጻር ያለውን ክፍተት ማስተካከል የቀጣዩ ወር የቤት ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች በሚፈለገው ልክ በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የክህሎት ስልጠናና ድጋፍ ማድረግም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የመጨረሻ ወርም አንድ ሺህ ለሚጠጉ ወጣቶች በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተመረቁት የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል፡፡