የምስራቅ ኢትዮጵያ የፀጥታ ሁኔታ ባለፉት ሦስት ወራት መሻሻል አሳይቷል

62

ጅግጅጋ  መጋቢት 15/2011 በምስራቅ ኢትዮጵያ የፀጥታ ሁኔታ ባለፉት ሦስት ወራት መሻሻል ማሳየቱን የአጎራባች ክልሎች የፀጥታ ምክር ቤት አስታወቀ።

በምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች የፀጥታ ምክር ቤት ሁለተኛ መድረክ በጅግጅጋ ከተማ ተካሄዷል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ጄኔራል ዘውዱ በላይ በመድረኩ ላይ  እንደተናገሩት ሕዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ ረገድ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በዚህም  የአካባቢው የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ መሻሻል እንደታየበት ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት በግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የተያዘውን ሥራ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ለአብነትም ከምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ወረዳ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀድሞው መኖሪያቸው ለመመለስ የተጀመረውን ጥረት ጠቅሰዋል።

መንግሥት ከፀጥታ  ኃይሎች ጋር  በመቀናጀት ተፈናቃዮችን መልሶ እንዲያቋቁም ጠይቀዋል።

ክልሎቹን ከግጭቶች ነፃ ለማድረግ በየደረጃው ያለው አመራርና የፀጥታ ኃይሎች ቀጣይነት ያለው ግንኙነት ማድረግ ወሳኝነት እንዳለውም አመልክተዋል።

የሶማሌ ክልል ፀጥታና ፍትህ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲ አዴል በበኩላቸው በቀጠናው የሚታየውን የፀጥታ ችግሮች እያባባሰ ያለው በግለሰብ ደረጃ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዘ የጦር መሳሪያ ጉዳይ እንዲተኮርበት ጠይቀዋል።

የአፋር ክልል ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድ አብዱ በክልላቸው የኢሳ ማህበረሰብ በሚኖርባቸው ልዩ ቀበሌዎች የሚከሰቱ ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው  በመሥራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላት አገራዊ ለውጡን  የሚያራምዱ ተግባራትን ለማከናወን ተስማምተዋል።

የፋፈንና የምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች ግጭቶች ለማስቆም ባደረጉት እንቅስቃሴ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ምክር ቤቱ ቀጣይ ስብሰባውን በሠመራ ከተማ እንዲያካሄድ ተወስኗል።

በመድረኩ የሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣አፋር፣የሐረሪ ክልሎችና የድሬዳዋ አስተዳደር የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች፣የዞኖችና ወረዳዎች አመራሮች እንዲሁም የምስራቅ ዕዝ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም