ኤጀንሲው ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምርት ደረጃ ለማሳወቅ ዝግጅት አድርጓል

85

አዲስ አበባ መጋቢት 15/2011 ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምርት ደረጃዋን ለላኪዎችና ለአባል አገራት ለማሳወቅ ዝግጅት ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ገለጸ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ ዝግጅቱ የተሟላ ባለመሆኑ አሁንም በትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስቧል።

የዓለም ንግድ ድርጅት 'ቴክኒካል ባሪየር ቱ ትሬድ'  የተሰኘ የደረጃና ጥራት ማረጋጋጫ እንዲሁም በአገራት ንግድ ላይ ጫና እንዳይፈጥሩ  ቀድሞ መሰራት የሚገባቸው ተግባራት ላይ ያተኮረ ስምምነት አለው።

የድርጅቱ አባል ለመሆን ከዓመታት በፊት ያመለከተችው ኢትዮጵያ የጥራት ደረጃንና ሌሎች መስፈርቶችን አሟልታ ባለመገኘቷ እስካሁን ከታዛቢነት የዘለለ ፈቃድ እንዳላገኘች መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ የደረጃ ዝግጅት ዳሬክተር አቶ ይልማ መንግስቱ ለኢዜአ እንደተናገሩት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የጥራት ደረጃና ፍላጎትን ለኢትዮጵያውያን ላኪዎች ለማሳወቅ የሚያስችለው ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ተግባር ተገብቷል።

ስለ ኢትዮጵያ ምርቶች የጥራት ደረጃ ለድርጅቱ አባል አገራት ማሳወቅ ሌላኛው የኤጀንሲው ተግባር ሲሆን በዚህ ላይም ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል። 

ደረጃዎች ሲዘጋጁ በዓለም የንግድ ድርጅት ህግ መሰረት መሆን አለበት፣ የተዘጋጁ ደረጃዎችንም ማሳወቅ ይጠበቅባታል።

የደረጃዎች ኤጀንሲም ደረጃ ሲያዘጋጅ በዓለም የንግድ ድርጅት ህግ መሰረት 60 ቀን ለአስተያየት አየር ላይ ማዋል አለበት።

በዚህም የሚመለከታቸው አገራትና ሌሎች በህጉ ላይ አስተያየት ያላቸው ባለድርሻ አካላት ለንግዱ እንቅፋት በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ አስቀድመው  አስተያየት ይሰጡበታል።

የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ኢትዮጵያ የምትከተለው የዓለም ንግድ ድርጅት ስምምነትና የደረጃ ዝግጅት፣ ግልጽነትና ሌሎች መስፈርቶችን የሚይዝ 'አይሶ ጋይድ 59' የተሰኘውን እየተገበረች ነውም ብለዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለሰ በበኩላቸው ኤጀንሲው እየሰራው ያለውና ደረጃን የተመለከቱ መረጃዎችን ለመስጠት ቢዘጋጅም ወደ ተግባር በመግባት በኩል ዘግይቷል ብለዋል።

ኤጀንሲው ለዓለም የንግድ ድርጅት አባልነትን በተመለከተ የሰራው ተግባር አሰራሩን ማቋቋም ብቻ ሳይሆን ከንግድ ጋር የተያያዙ የተለያዩ አገራት ህጎችና የኢትዮጵያ የጸደቁ ህጎችን መሰረት ያደረጉ መሆን አለባቸው።

ኤጀንሲው በሰው ሃይልና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ዝግጅት ቢያደርግም የተዘጋጁ ደረጃዎች በወረቀት በመሆናቸው መረጃዎችን ወደ ዘመናዊ አሰራር በመቀየር በኩል ክፍተት እንዳለውም አንስተዋል።

በመሆኑም ዘመናዊ የመረጃ አሰጣጥ ስርዓት መዘርጋትና የኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ደረጃዎችን መረጃ በቀላሉ እንዲገኙ በማስቻል በኩል ዝግጅቱን የተሟላ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የኤጀንሲው ሃላፊዎች በሰጡት ምላሽም የተደራጀ መረጃ ለማዘጋጀት ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን መረጃዎችን የማዘመንና የማሰራጨት ተግባር እየተሰራ ነው።

የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የንግድ ህግን ማዘመን ፣ በመንግስት የተያዙ የንግድ ተቋማትን ወደ ግል ማስተላለፍና ከምርት ጥራት ማረጋገጫ ጋር የተገናኙ  ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን የንግድ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ዝግጅት እያደረጉ እነደሆኑም መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም