ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ከፋፋይ ሀሳብ ማራመዳቸውና መንግስትም የሚናገረውን በተግባር አለማሳየቱ ለውጡን ስጋት ላይ ጥሎታል - ፖለቲከኞች

89

መጋቢት 15/2011 በሀገሪቱ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ህዝብን የሚከፋፍል ሀሳብ ማራመዳቸውና መንግስትም የሚናገረውን በተግባር አለማሳየቱ ለውጡን ስጋት ላይ ጥሎታል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ  የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናግረዋል።

ከዓመት በፊት በፖለቲካ አቋም እስራት፣ ስደትና አፈና የተለመደ መሆኑን የተናገሩት አመራሮቹ በህዝብ ግፊት የመጣው ለውጥ ለፖለቲካ ምህዳሩ መሻሻል እድል ፈጥሯል ነው ያሉት።

ከለውጡ በፊት ኢህአዴግ የፖለቲካ ምህዳሩን ሙሉ ለሙሉ ዘግቶት ነበር ያሉት የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት፤  በምርጫ ‘100% አሸንፊያለሁ’ በማለት ተፎካካሪዎቹን ማዳከሙን፣ የተለየ አስተሳሰብ ያላቸውን የራሱን አባላትና አመራሮች ጭምር ከመፈረጅ እስከ ማሰር መድረሱን ተናግረዋል።

ለፖለቲካ አፈናው እንዲረዳም የመረጃ ነጻነትና የሚዲያ አዋጅ፣ የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ምዝገባ አዋጅ ማውጣቱን በማሳያነት ይጠቅሳሉ።

ባለፉት ዓመታት ኢህአዴግ ሀገሪቷን ሲመራ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡና የተለያየ ሀሳብ ማስተናገድ አልመቻሉን በጥልቅ በተሀድሶ ግምገማ መለየቱን የሚገልጹት የኢህአዴግ የህዝብና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ ናቸው ።

በውስጠ ድርጅቱም የተለየ ሀሳብ የሚያነሳ አመራር ወይም አባል በሀሳቡ የተለየ መሆን ምክንያት ፍረጃና ግምገማ እንደሚደርስበት አስታውሰዋል።

በድርጅቱም  ሆነ በህዝብ ዘንድ  የዴሞክራሲያዊ ሂደቱን እያቀጨጨ መሆኑ በርካታ ጊዜ መነሳቱን የገለጹት አቶ ሳዳት፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ለውጥ በመግባት ምህዳሩን ለማስፋት ብዙ ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው ከአንድ ዓመቱ ለውጥ በፊት ስለብሔራዊ እርቅና መግባባት ሀሳብ ብናቀርብም መንግስት መስማት አልቻለም ብለዋል።

አቶ ተሻለ ሰብሮ

“ሀገራዊ እርቅን  ከመቀበል ይልቅ  ማን ከማን ተጣልቶ ነው እናስታርቅ የምትሉት? በአቋራጭ ስልጣን ፈልጋችሁ ካልሆነ በማለት ፖለቲከኞች ሲፈረጁ ነበር” ሲሉ አስታውሰዋል።

ከሶስትና አራት ዓመታት በፊት የታየው ተቃውሞ ኢህአዴግ ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠሩ ዶክተር ዐቢይን ወደ ሊቀመንበርነት ከማምጣትም ባሻገር ሌሎች ተስፋ ሰጪ ውሳኔዎችን ማምጣቱን የሚገልጹት ደግሞ  ኢንጅነር ይልቃል ናቸው።

ኢትዮጵያ አሁን በለውጥ ጎዳና ውስጥ ናት የሚሉት ኢንጅነሩ፤ እስረኞች መፈታታቸው፣ በውጭ ሀገር የነበሩና በሽብርተኝነት ተመዝግበው የነበሩ ሰዎች ወደ ሀገር መግባታቸው፣ ለመገናኛ ብዙሃን ነጻነት መሰጠቱ ለፖለቲካ ምህዳሩ መሻሻል ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የመንጋ ፍትህ መኖሩ፣ ወደ ክልሎች ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች መንቀሳቀስ አለመቻላቸው፣ የኢህአዴግ መዋቅር አለመለወጡ፣ የሀገር ውስጥ መፈናቀልና የዜጎች ያለመተማመን ፖለቲካዊ ለውጡን  ህዝቡ በጥርጣሬ እንዲመለከተው እያደረገ መሆኑንም ነው ኢንጂነር ይልቃል  የገለጹት።

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ በበኩላቸው አሁንም የመፈናቀል፣ የመገፋፋትና የዘረኝነት ፖለቲካ ለለውጡ ስጋት መሆናቸውን ነው ያነሱት፥።

በተለይም  አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ህዝብን ከመከፋፈል በመቆጠብ፤  በሰላማዊ መድረክ በመነጋገር ልዩነቶችን ማጥበብ ይገባቸዋል  ያሉት  አቶ ተሻለ፤  መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ የሚሰራውን ያህል ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የበኩላቸውን ማበርከት ይገባቸዋል ብለዋል።

ሀገር እንዳትረጋጋ፣ የተጀመረው ለውጥ ስር እንዳይሰድና ቀጣዩ ምርጫ ተዓማኒ  እንዳይሆን የሚሰሩ ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ጠይቀዋል።

የፖለቲካ ምህዳሩ ቢሰፋም በምክንያት መወያየት አለመጀመሩ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በለውጥ ሃይሉ የሚወራውና የሚሰራው መለያየቱ ህዝቡ ወደ ተስፋ ማጣት እየገባ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ኢንጅነር ይልቃል ናቸው።

የተወሰኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የራሳቸው ነጻ ሀሳብና አቋም ኖሯቸው የሀገሪቱን ችግሮች በመሰረታዊነት እየተነተኑ አማራጮችን አለማሳየታቸውን በድክመት አንስተዋል።

መገናኛ ብዙሃንም የፖለቲካ ምህዳሩ የተሻለ እንዲሆን ለመስራት አንጻራዊ ነጻነት ቢሰጣቸውም በተለያዩ ፖለቲካ ሃይሎች እጅ ላይ መውደቃቸው ሌላው ስጋት ነው ብለዋል።

የሀገሪቱ ፖለቲካ ከመጠላለፍ መውጣት እንዳለበትና “በሀገር ላይ መጠፋፋት ከተጀመረ ማንንም አይምርም” የሚሉት ኢንጅነር ይልቃል የፖለቲካ ምህዳሩንም ለማስፋት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።

የኢህአዴግ የህዝብና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሳዳት በበኩላቸው ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም ወደ ነበረችበት የፖለቲካ ችግር ለሚመልሱ ማናቸውም ጉዳዮች ዕድል መስጠት አይገባም ይላሉ።

ከዚህ ቀደም እንደነበረው ዓይነት የፖለቲካ ምህዳሩን ሊያቀጭጩ የሚችሉ አላስፈላጊ ጉዳዮች ከታዩ ከማንም በፊት ኢህአዴግ እርምጃ እንደሚወስድ የተናገሩት አቶ ሳዳት፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት እየተደረገ የአሰራር ስምምነት እስከመፈራረም መደረሱንም በማሳያነት አንስተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም