በአፍሪካ ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ መሰረታዊ ለሆኑት የግጭት ምንጮች መላ መዘየድ ያስፈልጋል

62

አዲስ አበባ  መጋቢት 15/2011 በአፍሪካ ዘላቂ ልማት ለማምጣት በአህጉሪቱ ለሚከሰቱ የግጭቶች መሰረታዊ ምንጮች መላ መዘየድ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለፀ። 

ይህ የተገለፀው 20ኛው የአፍሪካ አህጉራዊ ትብብር አሰራር ዘዴና 3ኛው የተባበሩት መንግስታት አህጉራዊ ዘላቂ ልማት ጥምረት ስብሰባ በሞሮኮ ሲካሄድ ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሃፊ አሚና መሐመድ በአህጉሪቱ የስደተኞችና ተፈናቃዮች ፈተናዎች ላይ በመምከር መፍትሄ ለማበጀት እየመከረ ላለው ጉባኤ ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር እንዳሉት አፍሪካ ዘላቂ ሰላምን ሳታረጋግጥ ልማትን ማሰብ አይቻላትም።

በመሆኑም አህጉሪቱ ለግጭት መንስኤ የሆኑ መሰረታዊ ምክንያቶችን በመለየት ሰላምን ለማስፈን መስራት ወደ ዘላቂ ልማት ለመሸጋገር ዓይነተኛው አማራጭ መንገድ መሆኑን አንስተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኢፍትሃዊነት ፍትሃዊነት ችግር መስፋፋት፣ የጾታ እኩልነት አለመረጋገጥ፣ የማህበረሰብ ትስስር ማነስ፣ ግጭት እና ሌሎች ምክንያቶች በአፍሪካ እያጋጠሙ ያሉ እንቅፋቶች መሆናቸውን ምክትል ጸሃፊዋ ጠቅሰዋል።

ለነዚህ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በጋራ መስራታቸውን መቀጠል አለባቸውም ብለዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ትብብር አሰራር ዘዴ በዘላቂ ልማት፣ በልማት እንዲሁም በሰባዊነትና ሰላም በአፍሪካ ውህደት እንዲኖር በማድረግ  የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማረጋገጥ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

አፍሪካ በአውሮፒያዊያን ቀመር 2030 እና በ2063 ለማሳካት ያስቀመጠቻቸውን የልማት አጀንዳዎች ከግብ ማድረስ የምትችለው መርሃ ግብሮቹን ማፋጠን ከቻለች ብቻ መሆኑን በመጠቆም በተቀናጀ ተግባር መፍጠን እንደሚገባ ተናግረዋል።

በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በምግብ እጥረት፣ በድህነትና ሌሎች ምክንያቶች አፍሪካ በህዝቦች መፈናቀል ከፍተኛውን ቁጥር በመያዝ ከአለም ቀዳሚ መሆኗን በማውሳት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ  እየተሰራ ቢሆንም መጠናከር አለበት ሲሉ ማሳሰባቸውን ኦል አፍሪካ ድረ-ገፅ ዘግቧል።

የተባበሩት መንግስታትም አለም ለኗሪዎቿ የተመቸች እንድትሆን እየሰራ ቢሆንም አገራት አጀንዳ 2030 ማሳካት በሚያስችላቸው አካሄድ ላይ ባለመሆናቸው ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሃፊ አሚና መሐመድ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም