በሀገሪቱ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

489

መቀሌ  መጋቢት 14/2011 በሀገሪቱ እያሽቆለቆለ የመጣውን የትምህርት ጥራት  ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡ 

በመቀሌ ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 28ኛው ሃገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ዛሬ ተጠናቅቋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የምዘና ጥናት ዳይሬክተር አቶ ይልቃል ወንድሜነህ በጉባኤ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እንደገለጹት ከአራት ዓመታት በፊት የአስረኛ እና  12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የትምህርት ጥራት ደረጃ  42 በመቶ ነበር። 

ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች በተመረጡ 306 ሺህ በሚሆኑ የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ በቅርቡ በተካሄደው ጥናትና በተሰጠው የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ፈተና ግን የጥራት ደረጃው  ወደ 32 በመቶ እንደወረደ ተረጋግጧል።

በእንግሊዘኛ  ቋንቋ  ማንበብ ፣ መጻፍና መናገር እንዲሁም በሌሎችም የትምህርት ዓይነቶች ተገቢውን የእውቀትና ክህሎት  ክፍተት መስተዋላቸው  የትምህርት ጥራት ችግሮች እንደሆኑ ተመልክቷል፡፡

በዚህም በተለይ ተማሪዎች ክፍተት ከሚያሳዩባቸው የትምህርት ዓይነቶች መካከል እንግሊዘኛ ፣ ፊዚክስ ፣ ባዮሎጂና ከሚስትሪ ይገኙበታል፡፡

የትምህርት ጥራት ችግሩ እስከ ታችኛው የትምህርት ደረጃዎች እንደሚታይ ተገልጿል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳመለከቱት የችግሩ ምክንያት ተብለው በባለሙያው ከተለዩ መካከልም ትምህርት ቤቶች መዘጋት፣ የትምህርት ሰዓታት በአግባብ ያለመጠቀም ፣ የመምህራን የስራ ትጋት ማነስ ይገኙበታል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ወላጅ ኮሚቴዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያለመወጣት ሌላው ክፍተት ነው፡፡

በመፍትሄነት የተመላከቱት ደግሞ አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ማድረግ፣ መምህርና ወላጆች ተቀናጅተው እንዲሰሩና የስራ ውጤታቸው በጋራ እንዲገመግሙ ማበረታታት  ናቸው።

” በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት የሚመደብ አስተማሪም ብቃቱና የተሰማራበት ሙያ ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል” ሲሉ  ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢው ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ በበኩላቸው በክልሉ ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚማሩ 4 ሚሊዮን 500 ሺህ  ተማሪዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም  ለተማሪዎች ቁጥር መጨመር እንደተሰራው  ሁሉ በትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ላይ እንዳልተደገመ አመልክተዋል፡፡

በትምህርት ባልበቃ ዜጋ  ሃገር ማልማትና ህዝብን የሚመራ  ማፍራት እንደማይቻል ገልጸው “ይህንን ለማሳካት ተጠያቂነት ያለበት አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል” ብለዋል።

” ያለ ሰላም የትምህርት ሽፋንና ጥራትን ማረጋገጥ እንደማይቻል ተረድተን  ልጆቻችን እንዲያውቁና ጊዜያቸውን በትምህርት ላይ እንዲያሳልፉ ተቀናጅተን መስራት ጀምረናል” ያሉት ደግሞ ከሶማሌ ክልል የመጡት  የትምህርት ወላጅ ኮሚቴ አመራር አባል ወይዘሮ ፋጡማ አብዲ ናቸው።

ለጥራት መረጋገጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚኖረው የትምህርት ግብአቶችን አቅርቦት ለማሻሻል የወላጅ ኮሚቴዎች ከክልሉ የትምህርት አመራሮች ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ የእቅድ ዝግጅት አስተባበሪ አቶ ጨላ አየለ በበኩላቸው፣ “የልጆቻችን ችግር ሳንፈታ የክልሎችና የሀገሪቱ ችግር መፍታት አይቻለንም ” ብለዋል፡፡

በዘርፉ ጠንክሮ በመስራት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በትጋት መስራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

እያሽቆለቆለ የመጣውን የትምህርት ጥራት  ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ሁሉም በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈለግ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታም እንዲተገበር ትምህርት ሚኒስቴር ሊያተኩርበት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

በጉባኤው ከፌዴራልና ከዘጠኝ ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ150 በላይ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡