የለገዳዲ የውሃ መስመር ላይ ስብራት ደረሰ

518

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2011 ከለገዳዲ አዲስ አበባ ከተዘረጉ ሁለት የውሃ መስመሮች አንደኛው ትናንት ምሽት መሰበሩን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ።

በመስመሩ መሰበር ምክንያት ከፊል የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች እስከ ማክሰኞ ድረስ ውሃ እንደሚቋረጥ ነው ባለስልጣኑ የገለጸው።

ባለስልጣኑ ለኢዜአ እንዳስታወቀው ከግድቡ ወደ ከተማዋ ውሃ ከሚያስገቡ ሁለት መስመሮች ባለ 900 ሚሊ ሜትር የሆነው ማስተላለፊያ መስመር ላይ ነው የመሰበር አደጋ የገጠመው።

የመስመሩ ስብራት ሰንዳፋ ጎሜ ቀለጻ በሚባል አካባቢ የተፈጠረ ሲሆን የአደጋው መንስኤ እስካሁን ያልታወቀ መሆኑን ነው የገለጸው። ሆኖም የደረሰው ስብራት ከፍተኛ መሆኑ ተረጋግጧል።

እስከ ፊታችን ማክሰኞ በተወሰኑ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች ውሃ በሙሉና በከፊል መቋረጡንና ስብራቱን ጠግኖ ወደ ስራ ለመመለስ ከፍተኛ ርብርብ በመደረግ ላይ መሆኑንም ነው ያስታወቀው።

ሙሉ ለሙሉ ውሃ የማያገኙ አካባቢዎች ሰሚት፣ መገናኛ፣ ሃያ ሁለት፣ ካዛንቺስ ፣ኡራኤል፣ ኮተቤ ፣ቦሌ ሚካኤልና አየር መንገድ አካባቢ ናቸው።

ተክለኃይማኖት፣ 6 ኪሎ፣ 4 ኪሎ፣ ፣ፒያሳ፣ ጥቁር አንበሳ አካባቢ ደግሞ ውሃ በከፊል የሚቋረጥባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡

ጥገናው ተጠናቆ መስመሩ ወደ ስራ እስኪገባ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም ባለስልጣኑ መልዕክቱን አስተላልፏል።