በምርምርና በትምህርታቸው ውጤታማ የሆኑ ሴት መምህራንና ተማሪዎች ተሸለሙ

598

ጎባ መጋቢት 14/2011 መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ሥራዎችና በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት መምህራንና ተማሪዎች እውቅናና ሽልማት ተሰጠ፡፡

ሽልማቱ ለበለጠ ሥራ ለመትጋት የሚያነሳሳችው መሆኑን መምህራንና ተማሪዎች ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው የስርዓተ ፆታ ቢሮ ኃላፊ  ወይዘሮ ጊሹ አደሬ በወቅቱ እንደገለጹት በሀገሪቱ እየተመዘገበ ባለው ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ እድገት ሴቶች ጉልህ ሚና አላቸው።

በዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር ሥራዎችና በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ 20 ሴት መምህራንና ተማሪዎች እውቅናና ሽልማት መበርከቱንም ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ጌሹ እንዳሉት ሴት መምህራንና ተማሪዎች ለተሻል ውጤትና ኃላፊነት እንዲበቁ ለማበረታታት ሽልማቱ እንዲበረከትላቸው ተደርጓል።

” ሴቶች በተለያዩ መስኮች በመሳተፍ ውጤታማ መሆን እንደምሚችሉ ሽልማቱ አንደ ማሳያም ነው ” ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ ተካ በበኩላቸው በተቋሙ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎን ለማሳደግ በተሰሩ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ሴት መምህራን በጥናትና ምርምር ሥራዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱንም አመልክተዋል።

“በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የሴት መምህራን ድርሻ 15 በመቶ ላይ ይገኛል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዘርፉ የተሳትፎ ደረጃቸውን ወደ 34 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

የአመራር ተሳትፏቸው በሚፈለገው መጠን አለማደጉን ጠቁመው ክፍተቱን ለመሙላት የአጭርና የረዥም ጊዜ እቅድ ተይዞ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተሸላሚ መምህራን መካከል ረዳት ፕሮፌሰር አይናለም ተሾመ ለደረሱበት ደረጃ የራሳቸው ጥረት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል ።

“በህይወቴ ያጋጠሙኝን ፈተናዎች በመቋቋምና የእውቀት አድማሴን በንባብ በማስፋት ውጤታማ ሆኟለሁ” ብለዋል ።

“ሴቶች እድል ካገኙ በሁሉም የሥራ ዘርፍ ውጤት ማስመዝገብ ይችላሉ” ያሉት ፕሮፌሰሯ የተሰጣቸው ሽልማትና እውቅና ለላቀ ሥራ እንደሚያነሳሳቸው ተናግረዋል ።

በመካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል የ5ኛ አመት ተማሪና 3 ነጥብ 9 ውጤት በማስመዝገብ ዘንድሮ ለመመረቅ የተዘጋጀችው ሰናይት ተፈራ  በበኩሏ ” ለስኬት የራስ ጥረት ወሳኝ ነው” ብላለች ።

“እችላለሁ በሚል መንፈስ ተስፋ ባለመቁረጥ ያሰቡበት ደረጃ መድረስ ይቻላል” ያለችው ተማሪ ሰናይት የተበረከተላት ሽልማት ለተሻለ ውጤት እንድትነሳሳ ብርታት እንደሚሆናት ገልጻለች ።

እንደ ተማሪ ሰናይት ገለጻ ዩኒቨርሲቲው ሴቶችን ለማብቃትና ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የጀመራቸውን የስልጠና የድጋፍ ዘርፎች ማስፋትና ማጠናከር ይኖርበታል።

“የላቃ ትኩረትና ቁርጠኝነት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት!” በሚል መሪ ቃል የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ስነ ስርዓት ላይ ውጤታማ ለሆኑ ሴት መምህራንና ተማሪዎች የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል ።

የባህል አልባሳትና ለምርምር ሥራ አጋዥ የሆኑ ቁሳቁስም በማበረታቻነት ተበርክቶላቸዋል ።

ዩኒቨርሲቲው በመደበኛና ተከታታይ የትምህርት መርሀ ግብር ከ20ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ሲሆን በተለያዩ መስኮች 100 የሚሆኑ ምርምሮችና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑም ታውቋል ።