በክልሉ የልማት ጥያቄን ፈጥኖ ለመመለስ ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ድጋፉን በተግባር ሊያረጋግጥ ይገባል --- ዶክተር አምባቸው መኮንን

50

ባህርዳር መጋቢት 13/2011  የአማራ ክልልን ህዝብ የልማት ጥያቄ ፈጥኖ ለመመለስ ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ድጋፉን በተግባር ሊያረጋግጥ እንደሚገባ  ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን አሳሰቡ።

ርዕሰ መስተዳደሩ በታክስ አምባሳደርነት ከተሾሙ የክልሉ  ተወላጆች ጋር ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተወያይተዋል።

የአማራ ህዝብ እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹና እህቶቹ  የጸጥታ፣የዴሞክራሲና የመልማት ጥያቄዎች አሁንም እንዳልተመለሱ ዶክተር አምባቸው  ተናግረዋል፡፡

መንግስት እነዚህን ጥያቄዎች በመመለስ ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችለው ከግብር ከፋዩ ህብረተሰብ በሚሰበሰብ ገንዘብ አማካኝነት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ዶክተር አምባቸው እንዳሉት " የአማራ ህዝብ እንደሌሎች ኢትዮጵያዊያን የቄሳርን ለቄሳር፣የእግዚአብሄርን ለእግዚአብሄር"  በሚል አስተሳሰብ ግብርን አለመክፈል እንደነውር የሚቆጥር ነው።

በተያዘው ዓመት 12 ቢሊዮን ብር ታክስ ለመሰብሰብ ታስቦ ባለፉት ሰባት ወራት 57 በመቶ ብቻ ማከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክልሉን ህዝብ ባህሪ በማይወክል መልኩ ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ተገቢውን ግብር ለመክፈል ወደ ኋላ የሚልበት  ሁኔታ መታየቱን ገልጸዋል።

ይህ ደግሞ ህሊናንና ህዝብን ማታለል በመሆኑ  ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በመክፈል  የክልሉ የልማት ጥያቄ ፈጥኖ ለመመለስ  ድጋፉን በተግባር ማረጋጋጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

"በሚቀጥሉት ሁለት ወራት የግብር አከፋፈል መጠኑን 90 በመቶ ለማድረስ በየደረጃው ያለው አመራርና ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ መረባረብ ይጠበቅበታል" ብለዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብዙአየሁ ቢያዝን በበኩላቸው በክልሉ በንግድ ስራ የሚተዳደር 306 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ቢኖርም በተለይ ለውጡን እንደመደበቂያ ዋሻ በመጠቀም ግብር የመክፈል ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ህዝቡ የክልሉ  የወደፊት የመልማት አቅም እንዳይረጋገጥ ፖለቲካዊ ተንኮል ያላቸው አካላት ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ግብሩን  እንዳይከፍል እየሰሩ መሆኑን ሊገነዘባቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኃላፊዋ እንዳሉት የግብር አምባሳደሮች ሚናም ስራ ተቆጥሮ የሚሰጣቸው ሳይሆን በያሉበት ዘርፍ ላይ ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው ህብረተሰቡ እንዳይሳሳት  ግንዛቤ መፍጠር ነው።

የምስራቅ ጎጃም ዞን የንግድ ማህበረሰብ ተወካይ አቶ ቆምጨ አምባው "እስከ መጋቢት 30 ቀን/2011ዓ.ም.  ድረስ በዞኑ ገጠር አካባቢ ህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ግብር ከፍሎ እንዲያጠናቀቅ የማግባባትና የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እየተሰራ ነው" ብለዋለ።

ህብረተሰቡ  በተሳሳተ መንገድ እየተሰበከ እንጂ ግንዛቤ ከተፈጠረለት ግብር ለመክፈል የማያቅማማና ግብር አለመክፈል እንደነውር የሚቆጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ተገቢውን ግብር ሳይከፍሉ ከመንግስት የሚፈልጉትን ነገር መጠበቅ ተገቢነት እንደሌለው የተናገሩት ደግሞ የሰሜን ጎንደር ዞን ግብር ከፋይ ህብረተሰብ ተወካይ ሀጁ ኑር ሁሴን ናቸው።

ህብረተሰቡም ይህንን ተገንዝቦ ተገቢውን ግብር እንዲከፍል ሰፊ የግንዛቤ ስራ መስራት እንደሚጠበቅ ገልጸው መንግስትን ለመሞገት መጀመሪያ ሁሉም የሚጠበቅበት ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።

" ስለሆነም የተሻለ ተቀባይነት አላችሁ የተባልን የግብር አምባሳደሮች የተጣለበንን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነን " ብለዋል።

በውይይት መድረኩ  የኃይማኖት አባቶች፣አርቲስቶችና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም