በቅርሶቹ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል በቅንጅት እንደሚሰራ ተጠቆመ

336

አክሱም መጋቢት 13/2011 በአክሱም ኃውልትና በአካባቢው የሚገኙ ቅርሶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል በቅንጅት እንደሚሰራ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በቅርሶቹ ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ለመከላከል በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአክሱም ከተማ ተካሂዷል፡፡

በሚኒስትሩ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ በእዚህ ወቅት እንዳሉት በአክሱም ኃውልት፣ በጥንታዊ መካነ መቃብሮችና በድንጋይ ላይ ጽሁፎች ጉዳት እየደረሰ ነው በሚል ከህዝቡ እየቀረበ ያለው ቅሬታ ትክክልና አግባብ ነው፡፡

“ቅርሶች ተጠብቀው ታሪካዊ ይዘታቸው ሳይቀየርና ሳይከለስ ተገቢ ጥገና ተደርጎላቸው ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ እንሰራለን” ብለዋል፡፡

አክሱም ዩኒቨርሲቲ፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣  የከተማው አስተዳደር ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ተቀናጅተው እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡

ሕብረተሰቡ ከቅርሶቹ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ለማሳደግ እንደሚሰራ የገለጹት አቶ ዮናስ፣ “የአክሱም ኃውልት ጥገና ሥራን በቅርቡ ለማስጀመር በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በቅርስነት በተከለሉ ስፍራዎች የሚገነቡት ህገወጥ ዘመናዊ ቤቶችን ለመከላከል ከከተማው ማዘጋጃ ቤትና ከነዋሪው ህዝብ ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ በአክሱማ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ተክላይ ገብረመድህን ናቸው፡፡

ለአክሱም ኃውልት መገኛ በሆነውና ጎቦድራ በተባለ ስፍራ ላይ በህገወጥ መንገድ ለኮንስትራክሽን ግብአት የሚሆኑ ምርቶችን የሚያመርቱ ሰዎች ላይ የህግ እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል፡፡

በውይይት መድረኩ “ቅርስ ከሕግ ማቀፍ ጋር ያለው ቁርኝት” እና “በአክሱም ከተማ የሚገኙ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቅርሶች የሚደረግላቸው እንክብካቤ” በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ወይይት ተካሂዷል፡፡

በአክሱምና አካባቢው ታሪካዊ ቅርሶች አደጋ ላይ መውደቅ የሚመለከታቸው አካላት ከህዝቡ ጋር ተናብበው አለመንቀሳቀሳቸው አንድ ምክንያት መሆኑን በመድረኩ ተነስቷል ።

በተመሳሳይ በአክሱም ከተማና አካባቢው የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች ተገቢ እንክብካቤ እያገኙ አይደለም፤ ትኩረትም አልተሰጣቸውም ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ቅሬታ ማንሳታቸውን ትናንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡