የለውጡ ስጋቶች ምንድ ናቸው?

43

አዲስ አበባ  መጋቢት 13/2011 በኢትዮጵያ የአንድ ዓመት የለውጥ ሂደት ውስጥ 'የተከተሉት የለውጡ ስጋቶች ምንድን ናቸው?' የሚለው ዛሬ በተካሄደው የ"አዲስ ወግ" የውይይት መርሃ ግብር ላይ በተደጋጋሚ ከታዳሚዎች የተነሳ ጥያቄ ነው። 

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተዘጋጀው በዚህ ውይይት ላይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ የመጡ ለውጦችና መሻሻሎች እንዲሁም ተግዳሮቶችን በተመለከተ የፖለቲካ ምሁራን፣ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ታድመዋል። 

በውይይቱ ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

"ለውጡ ምን ጥሩ ጎኖች አሉት? ስጋቶቹስ ምንድ ናቸው? ምንስ መደረግ አለበት? የሚለውን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች ለተወያይ ምሁራኑ ቀርበዋል።

  ለውጡ ከመጀመሪያ ጀምሮ በመጣበት ፈጥነትና በመጣበት ሁኔታ እዬሄደ ነወይ ? ባለፉት ሁለት ሶስት ወራት እየታዩ ያሉ ለውጦች አሁንም ወደ ብሄር ከረጢት እየተመለሰ አይደለም ወይ?

ክልሎች ሲፎካከሩ ኢትዮጵያን በሚጠቅም እነርሱን በሚጠቅም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ ሳይሆን 'የኔ ነው የኔ ነው' የሚል ነገር ታይቷል እንደዚህ አይነት ናሽናሊዝም በረከሰበት አገር ላይ እንዴት አድርገን ነው ሁላችንንም የሚያቅፍ ዴሞክራሲ የምንገነባው።

የኛ ሃገር 107 ፓርቲዎች ህዝቡን የሚያሳምኑበት ሃሳብ አላቸው ወይ?  ምን አይነት ዴሞክራሲ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ መመስረት ያለበት ? በአይዶሎጂ ላይ የተመሰረተ ወይስ ህዝቡ የሚሳተፍበት ኢትዮጵያዊያን በሙሉ እንዴት አድርገን ነው የምንገነባው?"  የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል

የመወያያ ሃሳብ ያቀረቡት ምሁራን በተሳታፊዎቹ የለውጥ አካሄድና ስጋትን በተመለከተ  ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ የታሪካዊ ዳራና ወቅታዊ ተግዳሮት በሚል ሀሳብ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው

 "በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ስርአት ቢፈጠር ጠቃሚ ነው ማለት ይቻላል ፣ለአብዛኛው ፖለቲካ ቡድንም ጠቃሚ ነው ነገር ግን በተግባር ሲታይ በአሁኑ ሰአት ያለው የፖለቲካ መከፈት ፣ነፃነቱን አስታኮ የተለያዩ ቡድኖች ቶ ዘማክሲመም በመሄድ የራሳቸውን፣የቡድን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ተጠቅመዋል ፣በሚያደርጉት ጥረት ባቋራጭ በሚወስዱት እርምጃ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የሩቁን ጊዜ ትልቁን የዴሞክራሲያዊ ሽግግር የሚባለውን የወል አላማ እየጎዱት እያሰናከሉት ይገኛሉ ይህንን በተለያዩ ቡድኖች በሚደረግ ሽኩቻ በቅርብ አስታውለናል።

ምሁራን ከላይ ለተነሱት ችግሮች ማን ምን ማድረግ አለበት የሚለውን የተለያዬ ሃሳብ የሰጡ ሲሆን፤ ከሃሳባቸው ውስጥ የሚከተለው ትልቁን ቦታ ይይዛል።

የፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪና መምህር ዶክተር ሰሚር የሱፍ  "በሚዲያዎች በኩል ያለው እንደገና በዚህ በአክቲቪስቶች በኩል ያለው ፈሩን ለቋል፣የመፈናቀልና ሌሎችም ነገሮች በተሰናዱ ወገኖች እየተደረጉ በመጡ ቁጥር ሁሉም ወደ ብሄር ቋቱ መደበቅና እንደገና ደግሞ የፌስቡክ ተኩሱ ወደምን ዞረ ብሄር ላይ እሚያጠነጥን ሆነ ይሄ ትንሽ መስተካከል ያለበትና አሁንም ደግሞ መንግስትና ሃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች ሊያስቡበት የሚገባ ነው። ብለዋል

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው  በበኩላቸው "የሚዲያ ነፃነትን በሚመለከት፣የፖለቲካ ምህዳር አቅራቢነቱን በሚመለከት፣ የፍይትህ ስረአቱ ወቅታዊ ተጨባጭ ለውጦችን በሚመለከት እነዚህ ነገሮች የሚደነቁ ነገሮች ናቸው ።ነገር ግን ወደ ዴሞክራሲ ገብተናል የሚያስብል ግን አይደለም ፣ለውጥ ውስጥ ስለሆነን ገና መሰራት ያለባቸው ብዙ ነገሮች አሉ ፣ሀገረ መንግስቱንና መንግስቱን ወጥነት ያለው ማድረግ ያስፈልጋል ፣ለሲቪል ሶሳይቲዎች እድገትና መጎልበት የበለጠ ሰፊ ሜዳ መክፈት ያስፈልጋል፣ተገዳዳሪ ሃይል እንዲነሳ ማስቻል ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ስራ ነው።የብሄር ክፍፍልንና ብሄርተኝነትን ኢትዮጵያን ናሽናሊዝም፣ኢትኒክ ናሽናሊዝም የምንቆጣጠርበት መንገድ አላበጀንም ማበጀት ያስፈልጋል፣ የሃብት ክፍፍልን በሚመለከት የነበረውን ኢ ፍትሃዊነት ማረም ያስፈልጋል። ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከያንዳንዱ ማህበረሰብ ጥረት ያስፈልጋል።"  ብለዋል

ምሁራኑ በተለይ አሁን የተፈጠረውን የፖለቲካ ምህዳር ባግባቡ በመጠቀምና ህዝቡንም ጭምር በሃገራዊ ጉዳይ ላይ በማሳተፍ ጠንካራ ፓርቲ እንዲፈጠር ማድረግም ዋናኛ ጉዳይ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በተለይ በኢትዮጵያ ምንነትና ታሪክ ላይ ያለው ልዩነት መግባባት ላይ መድረስ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ሲሉም መልሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም