በኢትዮጵያ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትንና የአካባቢ ንጽህናን ለማጠናከር የ6.5 ቢሊዮን ዶላር ፕሮግራም ይፋ ሆነ

123

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 በኢትዮጵያ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትንና የአካባቢ ንጽህናን ለማጠናከር እንዲቻል 'ዋን ወሽ' በሚል በ6.5 ቢሊዮን ዶላር የሚካሄድ የልማት መርሃ ግብር  ዛሬ ይፋ ሆነ።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዛሬ እንዳስታወቀው መርሃ ግብሩ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት በመላው ኢትዮጵያ ገጠርና ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃና አካባቢ ንፅህና ላይ በማተኮር ይተገበራል። 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መርሃ ግብሩን ይፋ ያደረገው "ማንም የንጹህ መጠጥ ውሃ ከማግኘት ወደ ኋላ መቅረት የለበትም" በሚል መሪ ቃል የዓለም የውሃ ቀንን ምክንያት በማድረግ በተሰናዳው ስነ-ሰርዓት ላይ ነው።

በዚሁ ወቅት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋግሾ እንደገለጹት ባለፉት አራት ዓመታት ተኩል ለሆነ ጊዜ በስምንት ክልልሎች የተተገበረው የመጀመሪያው ዙር ብሔራዊ ዋሽ መርሃ ግብር ውጤታማ ነበር።

መርሃ ግብሩ ከ3.6 ሚሊዮን በላይ የገጠርና ከተማ ህዝብን የንጹሁ ውሃ አቅርቦትና የአካባቢ ንፅህና ጥበቃ ተጠቃሚ በማድረግ በስኬት እየተተገበረ መሆኑን ዶክተር ነጋሽ ገልፀዋል። 

ዛሬ ይፋ የሆነውና ከመጪው በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው ሁለተኛው የዋን ወሽ መርሃ ግብር ይህንን ስኬታማ ውጤት በማስቀጠል የዜጎችን የንፁህ ውሃና አካባቢ ጤና ጥበቃን የበለጠ ለማስፋፋት አንደሚያስችል ነው ያመለከቱት።

በመጀመሪያው የዋን ወሽ መርሃ ግብር ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በዘርፉ የአቅም ግንባታ ላይ ያተኮረ ነበር። 

አዲሱ መርሃ ግብር ያለፈውን አጠናክሮ ከመቀጠል ባሻገር  ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ላይ በማተኮር ለመስራት ማቀዱ ከመጀመሪያው የዋን ወሽ መርሃ ግብር የተለየ እንደሚያደርገው የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዲኤታው ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ መሰረት በቂ ዝናብ በማያገኙና ውሃ ምንጭ ጉድጓድ በቀላሉ ማመንጨት በማይቻልባቸው አካባቢዎች እስከ 500 ሜትር ጥልቀት ያለው የውሃ ጉድጓዶች ይቆፈራሉ ሲሉም ገልፀዋል።

የወንዝ ጠለፋና ውሃ የማጣሪያ በቴክኖሎጂ አጥርቶ ለህዝቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያሰችሉ ተግባራትም የመርሃ ገብሩ አካላት መሆናቸውን ሚኒስትር ዲኤታው አመልክተዋል። 

መርሃ ግብሩ የአገሪቱ አጠቃላይ የንጹህ መጠጥ ውሃና አካባቢ ንፅህና አገልግሎትን 85 በመቶ ለማድረስ  የተያዘውን ትልም ለማሳካት መርሃ ግብሩ ዓይነተኛ ሚና አለው ተብሎ ታምኖበታል። 

ለልማት መርሃ ግብሩ የሚፈለገውን በጀት በመተባበር የሚሸፍኑት መንግስት፣ ከአጋር ድርጅቶችና ህብረተሰቡ ናቸው።

እስካሁን በተደረገው የሃብት ማሰባሰብ የቅድመ ዝግጅት ስራ አምስት መቶ ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር መሰብሰቡን አመልክተዋል።፡

ከብሔራዊ የዋን ወሽ አስተባባሪ ጽህፈት ቤት የፕሮግራሙን ሰነድ ያቀረቡት አቶ ከበደ ፋሪስ አዲሱ መርሃ ግብር በዘርፉ የነበሩትን የማስፈጸም አቅም ችግሮች ፈትሾ በመለየት መፈትሄ ለማበጀት ያስችላል ብለዋል።

ተገንብተው ለብልሽት የሚዳረጉ የውሃ መሰረተ ልማቶችን በተሻለ ቴክኖሎጂ ለማሻሻል፣ በግንባታው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና  ዝናብ አጠርና የውሃ አቅርቦት እጥረት ያለባቸውን አካባቢዎች ችግሮች ለማቃለልም መርሃ ግብሩ በትኩረት እንደሚሰራ ዶክተር ነጋስ ጠቅሰዋል። 

ለዚህም የሲቪክ ማህበራት፣መንግስት፣ የሚመለከታቸው አካላት፣ አበዳሪ ተቋማት፣ ለጋሽ ድርጅቶችና ተጠቃሚው ህብረተሰብ አስተዋጾኦና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ዋን ወሽ የዛሬ አራት ዓመት ተኩል የተጀመረ መርሃ ግብር  ሲሆን ከሌላው መሰል መርሃ ግብሮች የሚለየው መንግስት፣ አጋር ድርጅቶችና ተጠቃሚው ህብረተሰብ በሚያወጣው ሃብት የሚተገበር መሆኑ ነው ተብሏል።

የዓለም የውኃ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1993 ጀምሮ እየተከበረ ሲሆን በኢትዮጵያም በየዓመቱ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር መጋቢት 22 ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም